ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት መጠናከር ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት መጠናከር ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ደሴ ፤ጥር 18/2016(ኢዜአ)፡- ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት መጠናከር ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
የምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከወሎ፣ መቅደላ አምባና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር በደሴ ከተማ ምክክር እያካሄደ ነው።
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢና የሰሜን ምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል እንደገለጹት፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነትና አንድነት መጠናከር ሁሉም በየደረጃው የድርሻውን መወጣት አለበት።
በተለይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የጋራ ትርክቶችን በማጉላት፣ የአባቶችን የጋራ ጀግንነት በማስተማርና ትውልድን በማነጽ የጎላ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
እንዲሁም እርስ በእርስ ሊያግባቡ የሚችሉ ታሪኮቻችንን በማስተማር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት መጠናከር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም አንድነቱን በመጠበቅ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግና ለማጽናት ከሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁለንተናዊ ድጋፉንና ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በበኩላቸው፤ ምሁራን የኢትዮጵያ አንድነት፣ አብሮነትና የጋራ ትርክቶችን ማስተማር ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ምሁራን ችግሮችን በጥናት ጭምር በመለየት የመፍትሄ ሀሳብ በማቅረብ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመልካም አስተዳደርና ልማትን ጨምሮ ማንኛውንም ጥያቄ በውይይት፣ በንግግርና በሰላም መልስ እንዲያገኙ መስራት ከሁሉም እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ፤ ምሁራን የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ ተረድተው ለሰላሙ የመፍትሔ ሀሳብ እንዲያፈልቁ ምክክሩ መዘጋጀቱ ገልጸዋል።
በምክክሩ የሦስቱም ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሮችን በጥናት ጭምር ተለይተው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ እንሰራለን ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ከወሎ፣ መቅደላ አምባና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራን እንዲሁም የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።