የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው
አርባምንጭ ፤ጥር 18 / 2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው ።
"አርባምንጭ ታንብብ" በሚል መሪ ሀሳብ ለአርባ ምንጭና አካባቢዋ የተዘጋጀው መረሃ ግብሩ ለአራት ቀናት እንደሚቆይ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በቆይታው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተፃፉ የመጻህፍት አውደ ርዕይና የመጻሕፍት ሽያጭ እንደሚከናወን ተመልክቷል።
በመጻሕፍት፣ በሰነድና መዛግብት አስተዳደር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስነ-ጽሑፍ ክበብ ጋር ውይይቶች እንደሚደረጉም ይጠበቃል።
በተጨማሪም የስነ-ጽሑፍ መድረክ፣ በጋሞ ዞን ጨንቻ ማረሚያ ተቋም የመጻሕፍት ስጦታ እንዲሁም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት ምስረታ፣ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደሚኖርም ተመልክቷል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎትና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የጋሞና አርባምንጭ ከተማ አመራር አባላት ፣እውቁ ደራሲ ዘነበ ወላና ሌሎችም ደራሲያን እንዲሁም ነዋሪዎች ተገኝተዋል።