በአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ31 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ31 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
ባህር ዳር፤ ጥር 18 / 2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥና በልገሳ ከ31 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን የክልሉ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በክልሉ እስካሁን በጥሬ ገንዘብና በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው አስተዋጽኦ መደረጉን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።
የማስተባበሪያው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሃይለሚካኤል ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የህዳሴው ግድብ በመላው ህዝብ የነቃ ተሳትፎ የሚከናወን የዘመኑ ትውልድ የታሪክ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ነው።
በዚህም ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ላለፉት ዓመታት የክልሉ ህዝብ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ አሁን ካለበት ደረጃ እንዲደርስ ድርሻውን መወጣቱን አውስተዋል።
በዘንድሮው ዓመት 70 ሚሊዮን ብር ገንዘብ በቦንድ ሽያጭና በድጋፍ ለማስባሰብ ታቅዶ በተካሄደ እንቅስቃሴ እስከአሁን ከ31 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
የተሰበሰበው ገቢም ከግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከ90 በመቶ በላይና ከዓመታዊ እቅዱ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 45 በመቶ አካባቢ መሆኑን አስረድተዋል።
ክልሉ ወቅታዊ ችግር ቢያጋጥመውም ህዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ባለው ጉጉት የላቀ ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል በተግባር እያረጋገጠ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ይሄን ስኬት ማስመዝገብ የተቻለውም የክልሉን ህዝብና የመንግስት ተቋማት በማስተባበር ለመፈጸም የሚያስችል የአሰራር አቅጣጫ በመቀመጡ ነው ብለዋል።
በዚህም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚደረገው ጥረት የሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች ተግባሩን በሃላፊነት ወስደው መስራታቸው ለመጣው ውጤት አጋዥ ሚና መጫወቱንም አብራርተዋል።
የማስተባበሪያው ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ እንዳመለከቱት፤ ክልሉ የአባይ ወንዝ መነሻ እንደመሆኑ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ የአገልግሎት ጊዜውን ለማራዘም የሚያስችል የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና እንክብካቤ ላይ በጉልበቱ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በዚህም ከሃምሌ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከወንዙ መነሻ ጀምሮ በተካሄደው የአረንጓዴ ልማት አሻራና በጥር ወር 2016 ዓ.ም በተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በቀጣይም የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ዓመት ምክንያት በማድረግ የቦንድ ግዥ ሳምንትን በንቅናቄ በማካሄድ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአማራ ክልል የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን በጥሬ ገንዘብና በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው አስተዋጽኦ ማድረጉን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ አስታውሷል።