የአገልግሎቱና ሰራተኞቹ ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ ሃዋሳ ማዕከል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የአገልግሎቱና ሰራተኞቹ ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ ሃዋሳ ማዕከል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ
ሀዋሳ፤ ጥር 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና በሲዳማ ክልል የሚገኙ ሰራተኞቹ ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ ሃዋሳ ማዕከል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ፡፡
ድጋፉ ለማዕከሉ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰጥ ትራንስፎርመር ተከላ፣ የኤክትሪክ መስመር ዝርጋታና የቆጣሪ ወጪ የሸፈነ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ድሉ በወቅቱ እንደተናገሩት ሜሪ ጆይ የሚያከናውነው ሰብአዊ ድጋፍ የሁሉንም እርዳታ የሚጠይቅ ነው፡፡
አገልግሎቱ ባለፈው ዓመት በማዕከሉ ያደረገውን ጉብኝት ተከትሎ በቀረበለት ጥያቄ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግራቸውን መፍታት የሚያስችል ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡፡
በዚህም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የትራንስፎርመር ተከላ፣ መስመር ዝርጋታና ቆጣሪ የማስገባት ስራ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ በሲዳማ ክልል የሚገኙ የአገልግሎቱ ሰራተኞች ከደመወዛቸው ከ90ሺ ብር በላይ ድጋፍ በማድረግም የማዕከሉን የቆጣሪ ወጪ የሸፈኑት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል፡፡
አገልግሎቱ ለሜሪጆይ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው ፤ የተደረገላቸው ድጋፍ የማዕከሉን ገቢ ማስገኛ ስራ ለማስጀመር እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፤
ኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት ምክንያት ለአረጋዊያን አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖች ያለስራ መቆታቸውን አስታውሰው፤ የትራንስፎርመሩ መተከል በርካታ ችግሮችን ይፈታል ብለዋል፡፡
ለዘላቂ ድጋፍ የሚሆኑ ወፍጮ ቤት፣ የእንጀራና ዳቦ መጋገሪያ በመግዛት የገቢ ማስገኛ ስራዎችን በቅርቡ ለመጀመር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ሲስተር ዘቢደር ፤ ሜሪጆይ ከአረጋዊያን በተጨማሪ በጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ላይ የጀመረውን ስራ ለማጠናከር የኢትዮጵያዊንን ድጋፍ ይፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ተወካይ አቶ ደስአለኝ አብነው በበኩላቸው ለማዕከሉ ባደረጉት ድጋፍ ሰብአዊ ሃላፊነታቸውን እንደተወጡ ገልጸዋል፡፡
ሰራተኞችን በማስተባበር ለማዕከሉ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርጉና ሜሪጆይን መደገፍ ሰብአዊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ በማዕከሉ ድጋፍ የሚደረግላቸውን አረጋዊያንና የአገልግሎቱ ሰራተኛ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡