በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።
የመግባቢያ ስምምነቱ ዛሬ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት መካከል ተፈርሟል።
ስምምነቱ በዲጂታል ክህሎት አካታች ስትራቴጂ ጥናት ፣በዲጂታል ዘርፍ የቴክኒክ ስልጠና እና በዲጂታል ኢኖቬሽን ሀብት ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያስችላል ተብሏል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ 916 ሺ ስደተኞችን የዲጂታል ስርአቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቁሟል።
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላና በዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት የኢትዮጵያ የጅቡቲ፣የሶማሊያ፣የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ቀጠና ዳይሬክተር አሌክሶ ሙሲንዶ ፈርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ስደተኞችንና በአካባቢው የሚኖረውን ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምቹ የስልጠና እና የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ እኤአ በ2025 አሳታፊ ዲጂታል መር የኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም ለዚሁ ስኬት የሚረዳ ስራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል።
ስምምነቱ የዲጅታል መሰረተ ልማትን ለማሟላትና በሀገሪቱ ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች በዘርፉ ያላቸውን ክህሎት እንዲያሳድጉ የሚረዳ መሆኑን አንስተዋል።
የቀጠናው አገራት የአለም ሰራተኞች ድርጅት ተወካይ አሌክሶ ሙሲንዶ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው አካታች የዲጅታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ስደተኞች የዲጅታል ክህሎትን በማሳደግ የሚያጋጥማቸውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላትና የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ኮርፖሬሽን እና የሶማሌ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከአለም አቀፍ የስራ ድርጅት (ILO) ጋር በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ለስምምነቱ ተግባራዊነት የኔዘርላንድ መንግስትና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸው በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡