ጥምቀት በጋምቤላ - ኢዜአ አማርኛ
ጥምቀት በጋምቤላ

አብሮነት፣ ፍቅርና አንድነት የተሰበከበት የጥምቀት በዓል
የጥምቀት በዓል በጋምቤላ ደማቅ ትዕይንት አለው። ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ፣ ባህልና ትውፊትን እንደያዘ በልዩ ትዕይንት ይከበራል። ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ያሉት ታቦታት በከተራ ዕለት ወደ ባህረ ጥምቀቱ ስፍራ ባሮ ዳር ይወርዳሉ።
ከባህረ ጥምቀቱ ታቦታት ወደ መምበራቸው የሚመለሱት በየተራ በአምስት ቀናት ውስጥ ነው። በዚህ በልዩ ሁኔታ በሚከበረው በዓል ላይ ከልዩ ልዩ ሥፍራ የመጡ ምዕመናን ይታደማሉ።
በከተራ ዕለት የጋምቤላ ከተማ እጅግ ትዋባለች። ወጣቶች አካባቢያቸውንና ዋና ዋና መንገዶችን ያጸዳሉ፣ ሰንደቅ ዓላማ ይሰቅላሉ። ታቦታቱ ከመንበራቸው ሲወጡ በሆታና በእልታ ይታጀባሉ። ህዝበ ክርስቲያኑ በዝማሬ ምስጋና እያሰማ ይጓዛል።
በጋምቤላ የከተራና የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እጅግ በደመቀ ስነ- ስርዓት እየተከበረ ዓመታት አልፈዋል። የሃይማኖት አባቶች ምዕመናኑን ይባርካሉ፤ ያሰተምራሉ። መልዕክት ያስተላልፋሉ።
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በጋምቤላ የጥምቀት በዓል የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነትና በአብሮነት ደምቀውና አምረው የታዩበት ነው። ምዕመኑ ህዝበ ክርስቲያኑ ይህን መልካም እሴት አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም አፅንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የጥምቀት በዓል የፍቅር መገለጫ መሆኑንም ይናገራሉ። ቤተ ክርስቲያን ስለፍቅር የምትሰብክ፣ የምታስተምርና የምትመርቅ ናት ይላሉ።
በጥምቀት በዓል በጋምቤላ በቂርቆስ በዓል ላይ ተገኝተው ለምዕመናኑ ያስተላለፉት መልዕክት ስለመስማማት፣ ስለአንድነትና ስለፍቅር አጽንኦት የሚሰጥ ነው። በተለይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስና ሲላስ የሰበኩትን ፍቅር የምትሰብክ፣ ሃይማኖታዊ መልዕክቶች የሚተላለፍባት ናት ሲሉ ነው በአፅንኦት የገለፁት።
ከሰሞኑ አንድ የሲኖዶስ አባል የሆኑ አባት ሀይማኖታዊ አስተምህሮን ተፃረው፣ በክርስትናም ሆነ በሌላ ማንኛውም እምነት በማይደገፍ ሁኔታ ያደረጉት ገለፃ፣ እንዳሳዘናቸው ሲገልፁ፣ “ታቦት ወጥቶ አባት ይመርቃል እንጂ አይረግምም” ይላሉ።
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል፤ አንድ የሲኖዶስ አባል በአገረ አሜሪካ ተቀምጠው የአገሪቷን ጠቅላይ ሚኒስትር መርገማቸውን እቃወማለሁ ብለዋል።
ታቦት በወጣበት ስፍራ የሃይማኖት እሴትንና ፍቅርን መስበክ እንደሚያስፈልግ መልዕክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል፤ አሁን አሁን አንዳንዶች “ፖለቲካ ፖለቲካ እየሸተቱ ቤተ ክርስቲያኗን አበላሹብን” በማለት ተናግረዋል።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለአገር መሪ ትጸልያለች። የዚህ ዓይነቱ ጉዳይ “እኔን አይወክለኝም፤ ሀገረ ስበከቴን አይወክልም” በማለት ነው በጥምቀት በዓል ላይ ለተሳተፉት ምዕመናን ቤተ ክርስቲያን የፍቅር ሰባኪ መሆኗን ያወጁት።
የኢትዮጵያ ህዝብ አገር ለማፍረስ የተነሱትን “እየሰማህ ገደል እንዳትገባ እግዚያብሄር ከእናንተ ጋር ይሁን” ብለዋል።
ከጥምቀት በዓል ታዳሚዎች መካከል ዲያቆን ይፍረደው ጥሩነህ በሰጡት አስተያየት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ዝቅ ብሎ በመጠመቅ ትህትናን፣ ፍቅርን ፣አብሮነትን ያስተማረ በመሆኑ በዓሉን በዚሁ አግባብ አክብሬያለሁ ብለዋል።
በጋምቤላ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ብዙ ስላልተነገረለት እንጂ “የደመቀ በዓል ነው” ያሉት ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ይመር አዳነ፤ ወጣቱም ሆነ ጎልማሳው መልካም ነገሮችን በማካፈል፣ የአብሮነት እሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ በአንድነት በዓሉን እያከበረ ይገኛል።
ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ወጣት ጳውሎስ ፖል በሰጠው አስተያየት የጥምቀት በዓል ክርስቶስ በዓለም ላይ ያሉ የሰው ልጆችን ለማዳን ሲል የተጠመቀበት ታላቅ ዕለት መሆኑን ተናግሮ፤ በዓሉን በአንድነት፣ በመደጋገፍና በፍቅር እያከበረ መሆኑንም ገልጿል።
በከተራው ዕለት ወደ ባሮ ወንዘ የወረዱት ታቦታት በካህናትና በምዕመናን እጀባና ዝማሬ ወደ መንበራቸው የተመለሱ መሆኑም ታውቋል።