የግጭት መንስኤዎችን በመፍታት ለአካባቢያችን ሰላም፣ ልማትና እድገት በጋራ እየሰራን ነው- የዞኑ አርብቶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የግጭት መንስኤዎችን በመፍታት ለአካባቢያችን ሰላም፣ ልማትና እድገት በጋራ እየሰራን ነው- የዞኑ አርብቶ አደሮች
ጂንካ ፤ ጥር 17/2016(ኢዜአ)፡- የግጭት መንስኤዎችን በምክክር በማስቀረት ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገት በጋራ እየሰራን ነው ሲሉ የደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሮች ተናገሩ።
በዞኑ ሐመር፣ ዳሰነች፣ ኛንጋቶም እና ሳላማጎ አጎራባች ወረዳዎች ይገኛሉ።
ቀደም ሲል በወረዳዎቹ በግጦሽ ሳርና መሰል ምክንያቶች አልፎ አልፎ ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ችግሮች ይፈጠሩ ነበር።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአራቱ ወረዳ አርብቶ አደሮች ከግጭት ውድመት እንጂ የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ በመገንዘብ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ለአካባቢያቸው ሰላም፣ ልማትና እድገት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ የእንስሳት ግጦሽና ውሃ ለመጠቀም ሲባል ይፈጠሩ የነበሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቀረት የተፈጥሮ ሀብቶችን በጋራ የመጠቀም መርህ እየተከተሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የሐመር ወረዳ አርብቶ አደሮችን ወክለው ሀሳባቸውን የገለጹት አርብቶ አደር ዙቦ አይኬ "ቀደም ሲል አለመግባባቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ዱላ ስንማዘዝ ከርመናል" ብለዋል።
"ከግጭት ውድመት እንጂ ትርፍ እንደማይገኝ አሁን ተገንዝበናል" ያሉት አርብቶ አደሩ፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ግጭትን ከማስቀረት ባለፈ በሰላምና በልማት ሥራዎች በጋራ ለመስራት መወሰናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከግጭት ይልቅ ሰላምና ልማት ላይ ማተኮራቸውን ጠቁመው፣ በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በጋራ የመጠቀም መርህን እየተከተሉ መሆናቸውን በእዚህም ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለልማት እንጂ ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባ የገለጹት ደግሞ የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደር ተወካይ አቶ ማሞ ሎጴሬ ናቸው።
"የግጭት መንስኤ የሆኑ የጋራ ሀብቶችን በጋራ በመጠቀም በጋራ ማደግ ይቻላል" ብለዋል።
በአጎራባች ወረዳዎች መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ልምድን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና እድገት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
"በአካባቢያችን አበረታች የልማት ሥራዎች አሉ" ያሉት አርብቶ አደሩ፣ በሰላም ግንባታና በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አርብቶ አደሩ ችግሮችን በመመካከር የመፍታት የዳበረ ልምድ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የሳላማጎ ወረዳ አርብቶ አደር ተወካይ አቶ ሰሎኝ ኦይታጎኝ ናቸው።
ይህን የካበተ ልምድ በማጠናከር በአካባቢው ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
"በአሁኑ ወቅት የአጎራባች ወረዳ አርብቶ አደሮች በችግሮቻቸው ላይ መክረው መግባባት ላይ ለመድረስ ያሳዩት ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው፤ ይህን ማስቀጠል አለብን" ብለዋል።
"በአካባቢያችን የእንስሳት መኖን በመስኖ እንዲለማ መደረጉ በግጦሽ ሳር ምክንያት ሲከሰት የነበረውን ግጭት እያስቀረ ነው" ያሉት ደግሞ የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደር ተወካይ አቶ የራይታ ፒፒ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት በግጦሽ እና በውሃ ምክንያት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የተፈጥሮ ሀብቶችን በጋራ ለመጠቀም በአጎራባች አርብቶ አደሮች መካከል ከውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ወንድማማችነትን በማጠናከር ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም እና እድገት በጋራ እየሰሩ እንዳሉም ገልጸዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልኮ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ ያሉ አርብቶ አደሮች አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት የረጅም ዓመታት ልምድ አላቸው።
ይህን ልምድ በመጠቀም በአካባቢው ሰላምና ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተጀመረው የተቀናጀ ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በጋራ በማልማት ለመጠቀም የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።