ቀጥታ፡

በሀገር ቤት ቆይታችን በየአካባቢው የተከናወኑ አስደናቂ የልማት ሥራዎችን በአካል የማየት ዕድል ፈጥሮልናል

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፦  በሀገር ቤት ቆይታችን በየአካባቢው የተከናወኑ አስደናቂ የልማት ሥራዎችን በአካል የማየት ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ከተለያዩ አገራት የመጡ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን  ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ከባህላቸው ጋር እንዲተዋወቁ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት በመግባት የተለያዩ አካባቢዎችን እየጎበኙ ይገኛሉ።

በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የእንስራ የሸክላ ሥራና ሌሎችንም ጎብኝተዋል፡፡


 

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ነዒማ ሰሚር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ወደ ሀገር ቤት በመምጣቴ በአካል የተመለከትኳቸው የልማት ፕሮጀክቶች አስደንቀውኛል ብላለች።


 

በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሃቅ ለመረዳት በውጭ የሚኖሩ ወገኖች መጥተው መጎብኘት እንዳለባቸው ገልፃ፤ በሐሰት የሚናፈሱ ወሬዎችን ማመን የለብንም ብላለች።

በጉብኝቱ በኢትዮጵያ የሚያስደንቁ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አረጋግጫለሁ ያለችው ታዳጊዋ፤ ሀገራችን የሚፈለገውን እድገት ለማምጣት በትክክለኛው መንገድ ላይ ትገኛለች ብላለች።

ሌላኛው ወጣት ባኪ መቻሐ፤ በውጭ ሀገር ሆነን ስለ ኢትዮጵያ እንሰማ የነበረው አሉታዊ ገለፃ ስህተት መሆኑን በተግባር አረጋግጠናል ነው ያለው።


 

በእስካሁኑ ቆይታችን በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ አስደንቆናል ሲል ገልጿል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ የዓለም አገራት መካከል አንዷ መሆኗን በተግባር አረጋግጫለሁ ሲልም ተናግሯል።

በመሆኑም የሁላችንም ኩራት የሆነችውን ሀገራችንን በጋራ ማልማትና በምንችለው ሁሉ መደገፍ ይኖርብናል ብሏል።


 

በጉብኝቱ በቴክኖሎጂ ሽግግር ለኢትዮጵያ የበኩሌን አስተዋፅዖ እንዳበረክት ዕድል ፈጥሮልኛል ያለው ደግሞ ሌላኛው ወጣት ዮናስ ብርሃን ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም