የፍራፍሬ ምርትና የገበያ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ፋይዳ ለማጉላት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የፍራፍሬ ምርትና የገበያ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ፋይዳ ለማጉላት ትኩረት ተደርጓል
ሀዋሳ ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፡- የፍራፍሬ ምርትና የገበያ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ፋይዳ ለማጉላት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ ።
የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስቴር በሲዳማ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በፍራፍሬ ምርት ግብይትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሄዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ አበበ በፍራፍሬ ምርትና የገበያ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ችግሮቹን ለይቶ በመፍታት ዘርፉ ባለው አቅም ልክ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ፋይዳ እንዲኖረው ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር ፀባይና መልክዓ ምድር ለየትኛውም ምርት ምቹ እንደሆነ የገለፁት አቶ ደረጀ በሁሉም ክልሎች በተለይ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓዬና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ለማምረት የሚያስችል ሰፊ አቅም መኖሩን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ከምርቱ በተገቢው ልክ ተጠቃሚ ለመሆን ያልተቻለ ሲሆን በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለዘመናት ማነቆ ሆነው ቆይተዋል ብለዋል።
ለአብነትም በምርት አቅርቦት ላይ የሚታይ የጥራት ችግር፣ ግብይቱን ወጥ በሆነ መንገድ መምራት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ የኮንትሮባንድ ንግድና ሌሎች ችግሮች ተጠቃሚነቱ እንዳይኖር እንቅፋት መሆናቸውን ገልፀዋል።
የኮንትሮባንድ ንግድ ከምርት ጥራት ከማጓደል ባለፈ እንደ ሀገር ከፍተኛ ገቢን እያሳጣ መሆኑን አንስተው ለአብነትም ከ2011 እስከ 2015 ዓም ባሉት ጊዜያት ብቻ ከ1 ሺህ 140 ቶን በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጡ ተይዘው መወገዳቸውን አስረድተዋል።
የሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በሀገር ውስጥ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፤ የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘትና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ አካላት ተባብረውና ተቀናጅተው መስራት ለሀገራዊ ግብ መሳካትም ሆነ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው ለስኬቱም ክልሉ ተግባሩን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
ቢሮው ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን ከማከናወን ባለፈ አምራች አርሶ አደሩም ሆነ ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የሲዳማ ክልል ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በክልሉ 24 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት በአቮካዶ፣ በሙዝ፣ በፓፓዬና በሌሎች ፍራፍሬዎች የተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ ምርት እየሰጠ የሚገኘው 15 ሺህ ሄክታሩ እንደሆነ ገልፀዋል።
በክልሉ የፍራፍሬ ምርትና ግብይት ላይ ያልደረሱ ምርቶችን በመሰብሰብና በአያያዝ ጉድለት የሚስተዋል የጥራት ችግር መኖሩን ጠቅሰዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የወንዶ ገነት ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ነጌሶ ዋዪሶ በአንድ ሄክታር መሬት ከሚያለሙት አቮካዶ በዓመት ሶስት ጊዜ ምርት የሚሰበስቡ ሲሆን በአንድ ዙር ከ38 እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
እስካሁን ምርታቸውን ለሌሎች ነጋዴዎች እንደሚያስረክቡ ጠቅሰው በ"ልፋቴ ልክ ተጠቃሚ አይደለሁም" ብለዋል ።
በምክክር መድረኩ ላይ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ በዘርፉ የተሰማሩ የንግድ ተቋማት፣ አምራች አርሶ አደሮችና አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።