በኢትዮጵያ የግብርና ልማት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ልማትና እድገትን ማፋጠን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የግብርና ልማት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ልማትና እድገትን ማፋጠን ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የግብርና ልማት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ልማትና እድገትን ማፋጠን እንደሚገባ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የዩኒቨርስቲና ኢንዱስትሪ ትስስርን የሚያጠናክሩ ጥናትና ምርምሮችን ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታና በግብርናው ዘርፍ ያለውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም የተመለከተ ውይይት ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ፤ የግብርናውን ዘርፍ የሚያሳድጉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች ጥቅም ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ሮቦት) በትራክተር ማረስ፣ የመሬት ዝግጅትና የመሬት ጥንካሬና ልስላሴን የሚለይ፣ አረም የሚያርም፣ ማዳበሪያ መጥኖ የሚጨምር እንዲሁም አጨዳና ለቀማ የሚሰራ መሆኑን አስረድተው ለዘርፉ ልማት መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት በግብርናው ዘርፍ ጥቅም ላይ መዋሉ በልማቱ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ቴክኖሎጂዎቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።
የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ፤ በግብርናው ዘርፍ ያሉ የቴክኖሎጂ አማራጮች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በግብርና ምርቶች ላይ የሚያጋጥሙ በሽታዎችን የሚለዩና መፍትሔ የሚያመላክቱ ቴክኖሎጂዎች የሰውን ጊዜና ጉልበት መቆጠብ የሚያስችሉ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በግብርናው ዘርፍ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ይበልጥ ለመጠቀም የቅንጅት አሰራርን የሚጠይቅ መሆኑንም ነው ዶክተር ካሳሁን የገለጹት።
የዲጂታል ግሪን ፕሮጀክት ማናጀር ሰላማዊት ረታ፤ ከዚህ ቀደም በልማት ጣቢያዎች በመሄድ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ጊዜና ገንዘብን የሚፈጅ እንደነበር አመልክተዋል።
የግብርና ኢክስቴንሽን ስራውን በሚያግዝ የቪዲዮ ዲጂታል ኢክስቴንሽን አማካኝነት በተንቀሳቃሽ ምስል መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
በዲጂታል ግሪን ፕሮጀክት አማካኝነት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የበለጸገ "ፋርመር ዶት ቻት" የተሰኘ አርሶ አደሮች የምክር አገልግሎት የሚያገኙበትና ከመንግስት ጋር መረጃ የሚለዋወጡበት አማራጭ ተግባራዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረኩ እስከ ነገ ይቆያል።