ቀጥታ፡

አቶ ደመቀ መኮንን ከዩኒሴፍ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ) ፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ኢቲልቫ ካልዲሊ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም ፥ በቀጣይ ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዩኒሴፍ ለኢትዮጵያ በተለይም ለችግር ለተጋለጡ ህጻናት እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አድንቀዋል።

አክለውም፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


 

የዩኒሴፍ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ኢቲልቫ ካልዲሊ በበኩላቸው ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ለችግር ለተጋለጡ ህጻናት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ ህጻናት የሚያደርገው ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ምላሽ ላይ ከሚሰሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም