ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክርና መግባባት የምሁራን አበርክቶ ምን ሊሆን ይገባል?

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፦  'ለሀገራዊ ምክክርና መግባባት የምሁራን አበርክቶ' በሚል መሪ ሀሳብ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጁት ልዩ ጥናታዊ ሴሚናር ዛሬ ማለዳ ተካሂዷል።

በመድረኩ ስለ ሀገራዊ ምክክር ዕይታዎች፣ ልምድና ተሞክሮዎች እንዲሁም በሀገራዊ መክክር ሂደቶች የምሁራን ሚና የዳሰሱ የመወያያ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ምክክር በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት ችግሮቻቸውን በዘላቂነት መፍታትና ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ እምርታ ማምጣታችውን አንሰተዋል።


 

ኢትዮጵያም በዘመናት ታሪኳ ችግሮቿን እየፈታች ብትመጣም አሁንም ያልተሻገርናቸውና የማያግባቡን በርካታ ጉዳዮችን በምክክርና በውይይት መፍታት ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ በሂደት ላይ ላለው አገራዊ ምክክር ስኬታማነት ምሁራንን ጨምሮ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በተለይ ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ፤ የምክክር ሂደቱ በአጀንዳ ልየታ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።


 

የመወያያ አጀንዳዎች ልየታ ላይ ምሁራን አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመው፣ በመሆኑም የሚጠበቅባቸውን ተሳትፎና ትብበር ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ካቀረቡት መካከል ዶክተር ንጉሱ አክሊሉ፤ በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ለኢትዮጵያ መሻሻልና ለሀገረ መንግስት መጠናከር ሞጋች ምሁራን እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡


 

በሌላ በኩል ካለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ ምሁራን ከሞጋችነት ባሻገር በቀጥተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ በዝምታ እንዲሁም በአድርባይነት ባህሪ የሚገለጽ ተሳትፎ እንደነበራቸው አብራርተዋል፡፡

ያም ሆኖ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችል፣ ግልጽና አሳታፊ ምክክር እንዳልተደረገ ጠቁምው፣ ምክክር ቢደረግ ግን ተስፋ ሰጭ ምልክቶች እንዳሉ የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ውይይትን እንደማሳያ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ችግር ለሂደቱ ስጋት እንደሆነ በመጥቀስ፣ ከቃላት ጦርነት በመቆጠብ ሁሉም የራሱን አበርክቶ ማሳረፍ እንደሚገባው ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች አሳታፊነት እና ባለቤትነት ጉዳይ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ከኢትዮጵያ ዐውድ አንጻር መወሰድ እንዳለባቸው ያነሱት ዶክተር አንተነት ጸጋዬ ናቸው።


 

ኢትዮጵያ በሌሎች ሀገራት ምክክር ሂደቶች ተሞክሮዎች መማር እንዳለባት ያነሱት ምሁሩ፣ የምክክር ሂደቱን በራስ ባለቤትነት ብቻ መምራት፣ አጀንዳ ግልጸኝነትን መፍጠ እና በልሂቃን ተሳትፎ ብቻ አለመወሰን የሚሉ ቁምነገሮችን አንሰተዋለ።

ሌላው ፅሁፍ አቅራቢ አቶ አያሌው ዘገዬ በሀገራዊ ግጭቶች በዘላቂነትና በመሰረታዊነት የሚፈቱት በጠመንጃ ሳይሆን በምክክር እንደሆነ ገልጸዋል።


 

ህዝቡን ባለቤት ያደረገ ምክክርና መፍትሔ እንደሚያሻ ገልጸው፣ ምሁራን የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በፖለቲከኞች አሳልፎ መስጠት ሳይሆን የችግሮችን ምንጭ በቅጡ በማስረዳት በቁርጠኝነት ተሳትፏቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሀሳብን በሃሳብ የመሞገት ባህል እንዲዳብር ምሁራን በጥናትና በሃሳብ ሊደግፉት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ናቸው።


 

ምሁራንም ሀገራዊ ችግሮችን ከመሰረቱ በመፍታት ሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ብሎም የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ ለወመሰን በታለመለት ምክክር ሂደት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም