ቀጥታ፡

በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለማሳለፍ ከፍልሰት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ዲጂታይዝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፦ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለማሳለፍ ከፍልሰት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ዲጂታይዝ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናገሩ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢፌዴሪ የስደተኞችና የተመላሾች አገልግሎት፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር በዳታ መጋራት ስርዓት ዙሪያ እየመከረ ነው።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንደተናገሩት የፍልሰተኞችን መረጃ የማደራጀት ስራ የተጎጂዎችን መብትና ደህንነት ለማስከበርና መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ ለመስጠት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ።

ከመረጃ ቋት ግንባታ ጎን ለጎንም በመረጃ አመንጪና ተጠቃሚ መካከል የመረጃ ቅብብሎሹን ውጤታማና የተሳለጠ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በመሆኑም የስደት ተመላሽ ዜጎች መረጃ አያያዝና ልውውጥ ስርዓትን ውጤታማ ለማድረግና ዜጎችን የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ ችግር ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት እና አለም አቀፋዊ ስምምነቶችን የሀገሪቱ ህግ አካል በማድረግ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም