የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር በኤም-ፔሳ ደንበኞች ክፍያ የሚፈፅሙበትን አማራጭ ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር በኤም-ፔሳ ደንበኞች ክፍያ የሚፈፅሙበትን አማራጭ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር በኤም-ፔሳ ደንበኞች ክፍያ የሚፈፅሙበትን አማራጭ ይፋ አደረገ።
በዚህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጓዝ የሚፈልጉ ደንበኞች በኤም-ፔሳ ካሉበት ሆነው ክፍያ በመፈፀም መስተናገድ የሚችሉ መሆኑ ታውቋል።
የሳፋሪኮም ኤም-ፔሳ ድጅታል ክፍያ ስርአት በስልክ መተግበሪያ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት የሚፈጸምበት ሥርዓት ነው።
የአገልግሎቱን መጀመር አስመልክቶ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት በይፋ አስተዋውቀዋል።
የአየር መንገዱ ደንበኞች የአየር ትኬታቸውን ለመግዛት በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት በአየር መንገዱ ድረ-ገጽ ወይም በዓለም አቀፍ የጥሪ ማዕከል አማካኝነት በ''ኤም-ፔሳ'' ክፍያቸውን መፈጸም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ሳፋሪኮም ተደራሽነቱ ሰፊ በመሆኑ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ደንበኞችን በዚህ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መድረስ የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ ሆሊደይስና ዲጂታል አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ኃይለመለኮት ማሞ፤ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ፋይናንሲንግ ሥርዓትን በአገልግሎቱ ውስጥ በየጊዜው በማስረጽ የደንበኞቹ ምቾት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።
በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኤም-ፔሳ የክፍያ አማራጭ መኖሩ ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልና ለሁለቱም ተቋማት ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑ ተመላክቷል።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንሲንግ ዋና ኃላፊ ሚስተር ፓውል ካቫቩ፤ በአፍሪካ ግዙፉና ትርፋማ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በዲጂታል ፋይናንሲንግ የክፍያ ሥርዓት በጋራ ለመሥራት የተደረሰው ስምምነት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
በዓለም ላይ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት በስፋት እየተተገበረ በመሆኑ ለአየር መንገዱ ደንበኞችም ሆነ ለሳፋሪኮም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።