መንግሥት ከተሞች ተመጣጣኝ ልማትና እድገት እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ከተሞች ተመጣጣኝ ልማትና እድገት እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው
መቀሌ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፦ መንግሥት ከተሞች ተመጣጣኝ እድገት እንዲኖራቸው ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፋንታ ደጀን አስታወቁ።
ሚኒስትር ዴኤታው ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ከ10 ዓመታት በፊት አንድ ሺህ ያህል የነበሩ ከተሞች ብዛት አሁን ከ2 ሺህ 500 በላይ ደርሰዋል።
መንግሥትም እያደገ የመጣውን የከተሜነት ምጣኔና የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በአግባቡ እንዲመራና ከተሞች ደረጃውን የጠበቀና ተመጣጣኝ እድገት እንዲያመጡ ለማድረግ እየሰራ ነው።
ለዚህም በመሬት አስተዳደር፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ በቤቶች ግንባታና አቅርቦት ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑን አቶ ደጀን አስረድተዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በነበሩ ችግሮች የተጎዱ ከተሞችን መልሶ ለመገንባትና እድገታቸውን ለማፋጠን በተለየ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሁለንተናዊ የከተሞች እድገትና መሰረተ ልማት ዝርጋታ የተያዘውን እቅድና አቅጣጫ በየደረጃው ያሉት የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው የክልሉን ከተሞች መልሶ ለመገንባትና ለማነቃቃት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በክልሉ ዘጠኝ ከተሞች የመልሶ ግንባታና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
የክልሉ ከተሞችን መልሶ በማቋቋምና ደረጃ በደረጃ ''ስማርት ሲቲ'' ለመፍጠር ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የልምድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑንም ወይዘሮ አልማዝ ተናግረዋል።