የአፍሪካ ዋንጫን ሳቢና ተወዳጅ ያደረጉ አምስት ልዩ ገጽታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዋንጫን ሳቢና ተወዳጅ ያደረጉ አምስት ልዩ ገጽታዎች

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በ36 የምድብ ጨዋታዎች 89 ግቦችንና ያልተጠበቁ ክስተቶችን በማስተናገድ የጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ ደርሷል።
ያልተጠበቁ ሽንፈቶች፣ የኃያላን ብሔራዊ ቡድኖች ብርታት ማጣት፣ ተመጣጣኝ ፉክክርና ውጤት ቀያሪ የመጨረሻ ደቂቃ ግቦች 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫን ሳቢና ተወዳጅ ካደረጉት ልዩ ገጽታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የደጋፊዎች ባህላዊ ጭፈራዎችና በቀለም ያሸበረቁ አለባበሶች እንዲሁም የተደባላለቁ የደጋፊ ስሜቶችም ለአፍሪካ ዋንጫው ድምቀት ሰጥተውታል።
ውድድሩ "የምንጊዜውም ምርጥ የአፍሪካ ዋንጫ" የሚል ስያሜ እየተሰጠው ይገኛል።
በኮትዲቯር አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ትናንት ተጠናቀው ውድድሩ ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
24 አገራት በስድስት ምድብ ተከፍለው 36 ጨዋታዎችን አድርገዋል።
በምድብ ጨዋታዎች ከነበሩ ክስተቶች አምስት ቁልፍ የተባሉ ነጥቦችን እንመልከት።
እድለኛዋ ኮትዲቯርና ከውጥረት ተንፈስ ያለችው ካሜሮን
የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅ ኮትዲቯር በምድብ አንድ የተደለደለችው ከናይጄሪያ፣ ጊኒ ቢሳውና ኢኳቶሪያ ጊኒ ጋር ነው።
አዘጋጇ አገር ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏ ሰፊ ነው ተብሎ ግምት ቢሰጥም በጨዋታዎቹ የተገላቢጦሽ የሆነ ነገር ታይቷል።
ዝሆኖቹ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ጊኒ ቢሳውን 2 ለ 0 በማሸነፍ በውድድሩ ስኬታማ ጅማሮ አድርገዋል።
ይሁንና በሁለተኛው ጨዋታ በናይጄሪያ 1 ለ 0 መረታታቸው ስጋት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
በሶስተኛው ጨዋታ ኮትዲቯር የአገሪቷን የእግር ኳስ አፍቃሪ ደጋፊዎች አንገት ያስደፋ ሽንፈት አስተናግዳለች። በኢኮቶሪያ ጊኒ 4 ለ 0 ተሸነፈች።
ውጤቱን ተከትሎ ኮትዲቯር ከምድቡ የማለፏ ጉዳይ ከፍተኛ አጠባቂኝ ውስጥ የገባ ሲሆን በውድድሩ ብሔራዊ ቡድኑን ይዘው የቀረቡት የ70 ዓመቱ አንጋፋ አሰልጣኝ ጂን-ሉዊስ ጋሴት ከኃላፊነት ተነስተዋል።
ነገር ግን ትናንት በምድብ ስድስት ሞሮኮ ዛምቢያን 1 ለ 0 ማሸነፏን ተከትሎና ዛምቢያ በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ኮትዲቯር ተንጠልጥላ በሶስት ነጥብ ከምድቧ ጥሩ ሶስተኛ ሆና እንድታልፍ አድርጎታል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ዋንጫ የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ካሜሮንም ከምድቧ የማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ነበር።
የማይበገሩት አንበሶች በምድብ ሶስት በመጀመሪያ ጨዋታቸው አንድ አቻ ተለያይተው በሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ በወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ሴኔጋል 3 ለ 1 ተረትተዋል።
በዚህም ካሜሮን ወደ ጥሎ ማለፉ ለመግባት ጋምቢያን ማሸነፍ ግዴታዋ ነበር።
በጨዋታው የማይበገሩት አንበሶች በ85ኛው ደቂቃ የተቆጠረባቸው ግብ 2 ለ 1 እንዲመሩ ያደረገ ሲሆን ይህም ብሔራዊ ቡድኑን ከስንብት አፋፍ ላይ አስጠግቶት ነበር።
ይሁንና ካሜሮን በ87ኛው ደቂቃና መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በ91ኛው ደቂቃ ያስቆጠረቻቸው ግቦች 3 ለ 2 እንድታሸንፍ ያደረጓት ሲሆን ሴኔጋል ጊኒን 2 ለ 0 ማሸነፏን ተከትሎ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብታለች።
በአፍሪካ ዋንጫው ጥሩ ብቃት አላሳየም በሚል ትችት እየተሰዘነረበት ያለው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱ የተወሰነ እፎይታም ቢሆን ሰጥቷታል።
ወደ አገር ቤት የመመላሻ ትኬታቸውን በጊዜ የቆረጡት ጋና፣ አልጄሪያና ቱኒዚያ
34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እያስመለከተ ከሚገኛቸው ነገሮች አንዱ ከዚህ ቀደም ያለ ስኬትና ታሪክ ለወቅታዊ ብቃት ዋስትና እንደማይሆን ነው።
የአራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ጋና በነበረችበት ምድብ ሁለት ጥሎ ማለፍ ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ከተጠበቁ ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች።
ይሁንና በመጀመሪያ ጨዋታዋ በደሴቲቷ አገር ኬፕቨርዴ የደረሰባት ያልተጠበቀ የ2 ለ 1 ሽንፈት ጥቋቁሮቹ ኮከቦችን አስደንግጧል።
በሁለተኛ ጨዋታዋ መሻሻል በማሳያት ከግብጽ ጋር ሁለት ጊዜ መርታ ሁለት አቻ የተለያየች ሲሆን የተከላካዮች ድክመት ጋናን ዋጋ አስከፍሏታል።
በሶስተኛ ጨዋታዋ እስከ 90ኛው ደቂቃ 2 ለ 0 መርታ ወደ ጥሎ ማለፉ ገባች ሲባል በባከኑ ደቂቃዎች በተቆጠሩባት ጎሎች 2 ለ 2 ለመለያየት ተገድዳለች።
ውጤቱን ተከትሎ ጋና በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ብታጠናቅቅም ጥሩ ሶስተኛ ሆኖ ለማለፍ በቂ ባለመሆኑ ከአፍሪካ ዋንጫው ተሰናብታለች።
ውጤቱን ተከትሎ ጋና የ65 ዓመቱን እንግሊዛዊ አሰልጣኝ ክሪስ ሁተንን አሰናብታለች።
ሌላኛዋ ከአፍሪካ ዋንጫው በጊዜ የተሰናበተችው አገር የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ አልጄሪያ ናት።
በምድብ አራት የተደለደለችው አልጄሪያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከአንጎላ አንድ አቻ የተለያየች ሲሆን በሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ከቡርኪናፋሶ ሁለት እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርታለች።
የበረሃ ቀበሮዎቹ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታቸው ባልተጠበቀ መልኩ በሞሪታኒያ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግደው በሁለት ነጥብ የምድቡን ግርጌ ይዘው በማጠናቀቅ ከውድድሩ ተሰናብተዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጃሜል ቤልማዲ በገዛ ፈቃዳቸው ከአሰልጣኝነት ለቀዋል።
በምድብ አምስት የነበረችው ቱኒዚያም በአፍሪካ ዋንጫው የተሻለ ጉዞ ታደርጋለች ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
በመጀመሪያ ጨዋታዋ በናምቢያ ያልተጠበቀ የ1 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደች ሲሆን በቀጣዩ ጨዋታ ከማሊ ጋር አንድ ለአንድ ተለያይታለች።
ቱኒዚያ ወደ ጥሎ ማለፉ የመግባት ብቸኛ አማራጯ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታዋን ማሸነፍ ቢሆንም ትናንት ምሽት ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።
የካርቴጅ ንስሮች በመባል የሚታወቁት ቱኒዚያዎች ውጤቱን ተከትሎ በሁለት ነጥብ ከምድባቸው የመጨረሻውን ደረጃ በመያዝ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጃሌል ካድሪ ቱኒዚያ በጊዜ ከውድድሩ መሰናበቷን ተከትሎ በገዛ ፈቃዳቸው ከሀላፊነታቸው ለቀዋል።
የቴራንጋ አንበሶች የዋንጫ ክብራቸውን የማስጠበቅ ጉዞ
እ.አ.አ በ2021 በካሜሮን አዘጋጅነት በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል ግብጽን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉራዊውን ክብር ተቀዳጅታለች።
በኮትዲቯር አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫም ሴኔጋል በምድብ ሶስት ከካሜሮን፣ ጊኒና ጋምቢያ ጋር ተደልድላ ጨዋታዎቿን አድርጋለች።
የቴራንጋ አንበሶቹ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ጋምቢያን በላሚን ካማራ ሁለት ግቦችና በፓፓ ጉዬ አንድ ግብ ጋምቢያን 3 ለ 0 በማሸነፍ የዋንጫ ክብራቸውን የማስጠበቅ ጉዞ በድል ጀምረዋል።
ሴኔጋል በሁለተኛዋ ጨዋታ የአምስት ጊዜ የውድድሩን አሸናፊ ካሜሮንን 3 ለ 1 ረታለች። አምበሉ ሳዲዮ ማኔ፣ እስማይላ ሳርና ሀቢብ ዲያሎ የግቦቹ ባለቤቶች ናቸው።
በመጨረሻው የምድብ ጨዋታዋም በአብዱላዬ ሴክና በኢሊማን ንዳዬ ግቦች ጊኒን 2 ለ 0 በመርታት በዘጠኝ ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፉ የገባች ሲሆን በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች ያሸነፈች ብቸኛ አገር መሆን ችላለች።
ሴኔጋል በጨዋታዎቹ ያሳየችው ብቃት ለተከታታይ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ታነሳለች የሚለውን ግምት ያስጠበቀ ነው ማለት ይቻላል።
ሳይጠበቁ ታሪክ የሰሩ ብሔራዊ ቡድኖች
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እምብዛም ግምት ያልተሰጣቸው አገራት ትላልቅ የሚባሉ ቡድኖችን በማሸነፍ ጉድ አሰኝተዋል።
በምድብ አንድ ኢኮቶሪያል ጊኒ ኮትዲቯርን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፈችበት ውጤት እጅ በአፍ ያስጫነ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ ከሶስት ጨዋታ ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ ኢኮቶሪያል ጊኒ ከምድቧ አንደኛ ሆና አልፋለች።
በሶስቱ ጨዋታዎች አምስት ግብ ያስቆጠረው የኢኮቶሪያል ጊኒ የፊት መስመር ተሰላፊ ኢሚሊዮ ንሱዌ ሎፔዝ የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል።
ኢሚሊዮ ንሱዌ ሎፔዝ ኢኮቶሪያል ጊኒ 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ጊኒ ቢሳውን በረታችበት ጨዋታ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ በ34 ዓመት ከ110 ቀናት ዕድሜ ሀትሪክ በመስራት በእድሜ አንጋፋው ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፏል።
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአንድ ጨዋታ ሶስት ግብ ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋችም ነው።
በአፍሪካ ዋንጫው ሶስተኛ ተሳትፎዋን እያደረገች የምትገኘው ሞሪታኒያ አዲስ ታሪክ ጽፋለች።
በምድብ አራት የነበረችው ሞሪታኒያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ በቡርኪናፋሶ 1 ለ 0 እንዲሁም በሁለተኛ ግጥሚያዋ በአንጎላ 3 ለ 2 ተረታለች።
በሁለቱም ጨዋታዎች ሞሪታኒያ የተሻለ በቃት ያሳየች ሲሆን የራስ መተማመን ማጣትና የግብ እድሎችን አለመጠቀም ድክመቶች ሆነው ታይተዋል።
የ51 ዓመቱ የሞሪታኒያ አሰልጣኝ አሚር አብዱ ከአልጄሪያው የመጨረሻ ጨዋታ በፊት "እኛ ነጥብ አከፋፋይ አይደለንም አልጄሪያን እናሸንፋለን" ሲሉ ገልጸው ነበር።
በጨዋታው ላይ የታየውም ይሄው ነበር።
የ26 ዓመቱ መሐመድ ዴላሂ ያሊ በ37ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ሞሪታኒያ የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋን አልጄሪያን 1 ለ 0 አሸነፈች።
የቺንጉዌቲ አንበሶች የሚል ተቀጽላ ስም ያለው የሞሪታኒያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ድሉን በማስመዘገብ በጥሩ ሶስተኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።
የደቡብ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናምቢያም በውድድሩ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገች የምትገኝ ሀገር ናት።
በምድብ አራት የነበረችው ናምቢያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ የአንድ ጊዜ የውድድሩን አሸናፊ ቱኒዚያን የአማካይ ተጫዋቹ ዲኦን ካቬንጂ ባስቆጠረው ግብ 1 ለ 0 በመርታት ያልተጠበቀ ውጤት አስመዝግባለች።
በሁለተኛ ጨዋታው በደቡብ አፍሪካ 4 ለ 0 በሆነ ውጤት የተራተች ሲሆን ትናንት በምድቧ ባደረገችው የመጨረሻ ጨዋታ ከማሊ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።
ውጤቱን ተከትሎ ናምቢያ በአራት ነጥብ በምርጥ ሶስተኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባት ችላለች።
በምድብ ሶስት ከምድቧ ባታልፍም ጋምቢያ በካሜሮን 3 ለ 2 በተሸነፈችበት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ያሳያቸው ተጋድሎና ብቃት በእግር ኳስ ተመልካቾች አስወድሷታል።
ጋምቢያ በጨዋታው እስከ 85ኛው ደቂቃ 2 ለ 1 በመምራት የካሜሮንን ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት ሕልም ልታጨልም ነበር።
የእግር ኳስ ተመልካቾችና ተንታኞች በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እየታየ ባለው ፉክክር "ትንሽ ሀገርና ብሔራዊ ቡድን የለም ማንንም ከግምት በታች ማድረግ አይገባም" የሚለውን ነገር ያስተማረ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።
በ36 ጨዋታዎች 89 ግቦች 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በጎሎች የተንበሸበሸ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ጨዋታ ለመመልከት ወደ ሜዳ ለሚገባው ተመልካች እርካታን የሚፈጥር ነው።
በምድብ ውድድር በተደረጉ 36 ጨዋታዎች 89 ጎሎች ከመረብ ላይ አርፈዋል። ይህም ማለት በአማካይ 2 ነጥብ 4 ግቦች ከመረብ ላይ ያርፋሉ ማለት ነው።
ከ36ቱ ጨዋታዎች 21ዱ በመሸናነፍ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን 15 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተደምድመዋል።
በምድብ መርሐ ግብሩ ግብ ያልተቆጠረባቸው ጨዋታዎች ብዛት ሶስት ነው።
በአፍሪካ ዋንጫው እስከ አሁን ከፍተኛ ግብ የተቆጠረበት ጨዋታ በምድብ አንድ ኢኮቶሪያል ጊኒ 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ጊኒ ቢሳውን ያሸነፈችበት ጨዋታ ነው።
በአፍሪካ ዋንጫው በሰፊ የግብ ልዩነት የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ሁለት ሲሆኑ ኢኳቶሪያል ጊኒ አዘጋጅ ሀገር ኮትዲቭዋርን እንዲሁም ደቡብ አፍሪካን ናምቢያን 4 ለ 0 የግብ ልዩነት አሸንፈዋል።
በአፍሪካ ዋንጫው እስከ አሁን ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረችው አገር ኢኮቶሪያል ጊኒ ስትሆን ዘጠኝ ጎሎችን ከመረብ አገናኝታለች።
በምድብ ጨዋታዎች በርካታ ግቦች ያስተናገዱት አገራት ጊኒ ቢሳውና ጋምቢያ ናቸው። ሁለቱ ሀገራት በተመሳሳይ ሰባት ጎሎች ተቆጥሮባቸዋል።
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉት 24 ሀገራት በሙሉ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከጥር 18 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ይከናወናሉ።