በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብርቱ ፉክክር የሚደረግባቸው ጨዋታዎች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብርቱ ፉክክር የሚደረግባቸው ጨዋታዎች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፦ በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቻል ከፋሲል ከነማ እና ባህርዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠበቃሉ።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በዛሬው ዕለት በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚጀመር ሲሆን ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ኢትዮጵያ መድንና ሻሸመኔ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚሰለጥነው ሻሸመኔ ከተማ፤ በ11ኛው ሳምንት የፕሪሚየርሊጉ ጨዋታ ሀምበሪቾ ዱራሜን 3 ለ 0 በማሸነፍ የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ድሉን ማስመዝገቡ ይታወሳል።
ከምሽቱ 12 ሰዓት ደግሞ በ26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ በፕሪሚየርሊጉ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቻል ከፋሲል ከነማ ይጫወታል።
በማስቀጠልም ዓርብ ዕለት በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ በ26 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ ከሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በዚሁ ቀን በአዳማ ከተማና በሐዋሳ ከተማ መካከል የሚደረገው ጨዋታም ምሽት 12 ሰዓት የሚከናወን ይሆናል።
የ12ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ ሲቀጥሉ፤ ቅዳሜ በሊጉ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የአምናው የዋንጫ ባለቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬደዋ ከተማ ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት ይጫወታሉ።
በዚሁ ቀን ሲዳማ ከሀምበሪቾ ዱራሜን ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ደግሞ እሁድ ከቀኑ 9 ሰዓት ጨዋታቸውን ሲያደርጉ፤ ምሸት 12 ሰዓት ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ዲቻ ይጫወታሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሠንጠረዥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መቻል በ26 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ሲመሩ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ21 ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የከፍተኛ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው በ8 ጎል ሲመራ፣ የመቻሉ ምንይሉ ወንድሙ፣ የፋሲል ከነማው ጌታነህ ከበደ እና የወላይታ ዲቻው ብንያም ፍቅሩ እያንዳንዳቸው በአምስት ጎሎች ይከተላሉ።