ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁነኛ መፍትሄ ነው- ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2016(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ።

ለሀገራዊ ምክክርና መግባባት የምሁራን አበርክቶ በሚል መሪ ሀሳብ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጁት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው መድረክ የሁለቱ ተቋማት አመራሮችና ምሁራን የተገኙ ሲሆን የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ በዓለም ላይ በርካታ አገራት በሀገራዊ ምክክር ችግሮቻቸውን በዘላቂነት መፍታት መቻላቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በዘመናት ታሪኳ ችግሮቿን እየፈታች ብትመጣም አሁንም ያልተሻገረቻቸውና የማያግባቡ በርካታ ጉዳዮችን በምክክር መፍታት ይጠይቃል ብለዋል።


ለተግባራዊነቱም  ጥቂት ልሂቃን ባቻ ሳይሆን ምሁራንን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ማሳተፍ  አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት በተለይም የምሁራን ተሳትፎና እገዛ የላቀ ሚና ያለው በመሆኑ የድርሻቸውን አንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የውይይት መድረኮችን በማካሄድ የበኩሉን ሚና የሚወጣ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክሮች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ፤ የምክክር ሂደቱ የአጀንዳ ልየታ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

የመወያያ አጀንዳዎች ልየታ ላይ ምሁራን ልዩ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመው፣ ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ትብብርና ተሳትፎአቸውን አንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም