በተሽከርካሪ አደጋ   የ14 ሰዎች  ህይወት አለፈ

 

ደሴ ፤ ጥር 15/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ በተከሰተ የተሽከርካሪ አደጋ የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የደሴ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር መሃመድ ሰይድ ለኢዜአ እንዳሉት አደጋው የደረሰው በወረዳው 013 ቀበሌ ዛሬ ከቀኑ 6 ሰአት ተኩል አካባቢ ነው ።

ከደሴ ወደ አቀስታ ከተማ  20 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3-46660 አማ የሆነ አነስተኛ የህዝብ  ማመላለኛ ተሽከርካሪ ገደል በመግባቱ የ14 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ከሟቾቹ መካከል የ12ቱ ሰዎች ህይወታቸው ወድያውኑ ሲያልፍ አንዱ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ ባለበት ወቅትና  ሌላው ተሳፋሪ ደግሞ ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  ከደረሰ በኋላ ህይወቱ ማለፉን አብራርተዋል።

ከአጠቃላይ ሟቾች ውስጥም ስድስቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሽከርካሪውን ጨምሮ ሌሎች በአደጋው ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው  ስድስት ሰዎች  በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከሟቾች ውስጥ እስካሁን የስምንቱ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱንና የቀሪዎቹ አስከሬን ቤተሰቦች እየተጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ፖሊስ አደጋውን መንስኤ እያጣራ መሆኑን  ኮማንደር መሃመድ  አስታውቀዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም