መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ የዳረጉት የአዘዞ-ጎንደር እና ጎንጂ-ቆለላ የመንገድ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ ሊጠናቀቁ ይገባል- ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ የዳረጉት የአዘዞ-ጎንደር እና ጎንጂ-ቆለላ የመንገድ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ ሊጠናቀቁ ይገባል- ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ ፤ ጥር 15/2016 (ኢዜአ)፦ በግንባታ መጓተት መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ የዳረጉት የአዘዞ-ጎንደር እና ጎንጂ-ቆለላ መንገድ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ እንዲጠናቀቁ በህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዘዞ-ጎንደር እና ጎንጂ-ቆለላ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የ2014/15 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።
በፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር አበራ ታደሰ፤ በግንባታ ሂደቱ ላይ ከካሳ ክፍያና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የግንባታ ፕሮጀክቶቹ መጓተታቸውን ገልጸዋል።
ይህም በህዝብና መንግስት ሀብት ላይ ብክነት ማስከተሉን ነው የተናገሩት፡፡
ለአብነትም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የወሰን ማስከበር ስራ ሳያከናውን ከኮንትራክተሮች ጋር ውል በመፈራረሙ ኮንትራክተሩ ወደ ስራ ሳይገባ የቆየበትን የ9 ሚሊየን ብር ካሳ እንዲከፍል ማድረጉን ተመላክቷል፡፡
ይህም 12 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው የጎንደር- አዘዞ አስፓልት መንገድ ግንባታ በሁለት ዓመታት መጠናቀቅ ሲገባው አምስት ዓመት መቆየቱን ገልጸዋል።
በኦዲቱ የተገኘው ግኝት መሰረት ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ወጪ ከመጠየቅ ባሻገር በአካባቢ ነዋሪዎች ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ጎንጂ-ቆለላ ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ከስድት ወር ለማጠናቀቅ እቅድ በ2012 ዓ.ም ቢጀመርም እስካሁን አለመጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ በዋናነት ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ እንደተጓተተ በኦዲት ግኝቱ መመላከቱን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም በግንባታ መጓተት ምክንያት መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ የዳረጉት የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ችግራቸው ተፈትቶ በአፋጣኝ እንዲጠናቀቁ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን በበኩላቸው ለፕሮጀክቶቹ የተጠየቀው የወሰን ማስከበር ካሳ ክፍያ የተጋነነ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይህን ለማስተካከልም አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱንም ነው የተናገሩት፡፡
የአዘዞ-ጎንደር መንገድ አሁን ከ60 በመቶ በላይ አፈጻጸም ላይ መድረሱንና እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ንጣፍ ይከናወናል ብለዋል።
የጎንጂ-ቆለላ መንገድ ደግሞ ከ71 በመቶ በላይ ግንባታ መጠናቀቁን ገልጸው ቀሪውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በክዋኔ ኦዲቱ የተገኙ ግኝቶችን በቀጣይ ለማስተካከልና ቀሪውን ግንባታ ለመጨረስ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡