ቀጥታ፡

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ከመቀየር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አስገኝቶልናል --- አርሶ አደሮች

ወልዲያ ፤ ጥር 15/2016 (ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በሰሯቸው የፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ከመቀየር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ቀሜታ ማስገኘቱን በወልዲያ ከተማ የገጠረ ቀበሌዎች  አርሶ አደሮች ገለጹ።

 በከተማ አስተዳደሩ በአደንጉር የገጠር ቀበሌ የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ተጀምሯል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አምባዬ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አካባቢያቸው በተራራ የተከበበ በመሆኑ የእርሻ ማሳቸው ለም አፈር በየዓመቱ በጎርፍ እየተወሰደ ለምነቱን ሲያጣ ቆይቷል።

ከዚህም ባለፈ ከተራራው የሚነሳው ጎርፍ በመኖሪያ መንደራቸው ሰብሮ በመግባት ክረምት በገባ ቁጥር ለችግር ያጋልጣቸው እንደነበር ገልፀዋል።

ችግሩን ለመፍታት ባለፉት 12 ዓመታት በተከታታይ በተሰራ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ተራራው በማልማቱና በእጽዋት በመሸፈኑ የቀደመው ችግር መፈታቱን ጠቁመዋል።

የጎርፍ መነሻ የሆነው ተራራ በአግባቡ በመልማቱም የእርሻ ማሳቸው ለምነቱ በመጠበቁ የሰብል ምርት እድገት ከማስገኘቱም ባለፈ ለቤት እንስሳት በቂ መኖ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ያገኙትን ጠቀሜታ ለማስቀጠልም በዚህ የበጋ ወራት የልማት ስራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

''ቀደም ሲል በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ተጠቃሚ ሆነናል" ያሉን ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ የሺ ደምሴ ናቸው።

ቀደም ሲል ውሃ ለመቅዳት አስቸጋሪ ገደላማ ቦታ ለመሄድ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው፤ ''ዛሬ በቅርባችን  በጋና ክረምት የሚያገለግሉ ምንጮች ፈልቀውልን እፎይታን አግኝተናል'' ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ስራዎች የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በማስፋትም በዚህ የበጋ ወራት የተጀመረውን የልማት ስራ እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቀዋል።

የወልዲያ ከተማ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ደስታ ሞላ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ስራ በአምስት ተፋሰሶች ውስጥ በ2 ሺህ 699 ሄክታር መሬት ላይ ይከናወናል ብለዋል።

''ይህን ስራ ስኬታማ ለማድረግ በ84 ልማት ቡድን የተደራጀ ሁለት ሺህ የሰው ኃይል ወደ ስራ ገብቷል'' ያሉት ሃላፊዋ ስራው ውጤታማ እንዲሆንም ተገቢው የሙያ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

ቀደም ሲል በለሙ ተፋሰሶች ውስጥም 100 ወጣቶችን በንብ ማነብ ስራ ለማሰማራት የልየታ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ወጣቶቹን ወደ ስራ ለማስገባት 10 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት በ55 ሄክታር መሬት ላይ በተሰራ የተፈጥሮ ሃብት ስራ 200 ሺህ ችግኞች በመትከል በተደረገ እንክብካቤና ጥበቃ 76 በመቶ ማፅደቅ እንደተቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም