የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃ ግድቦችን ከደለል አፈር ለመጠበቅ ለአፈርና ውሃ እቀባ ተግባር ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃ ግድቦችን ከደለል አፈር ለመጠበቅ ለአፈርና ውሃ እቀባ ተግባር ትኩረት ተሰጥቷል
ጎንደር ፤ ጥር 15/2016(ኢዜአ)፦የጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ ግድቦችን ከደለል አፈር ለመጠበቅ በተፋሰሶች አካባቢ ለአፈርና ውሃ እቀባ ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ተግባር መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ አስራ አንድ የገጠር ቀበሌዎች የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ለማካሄድ ስራው ዛሬ በሳይና ሳቢያ ቀበሌ ተጀምሯል፡፡
በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ አቶ አስቻለው ወርቁ እንደተናገሩት፤ የአንገረብና የመገጭ የመጠጥ ውሃ ግድቦችን ከደለል አፈር ለመታደግ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረጉ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በዘንድሮ በጋ ወራትም በተመረጡ 18 ተፋሰሶች በ617 ሄክታር ላይ የእርከንና ክትር ስራዎች በማከናወን የመጠጥ ውሃ ግድቦቹን ከደለል አፈር የመታደግና ከተማውንም ከጎርፍ አደጋ የመከላከል ተግባራት መከናወናቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ የመጠጥ ውሃ ግድቦች በሚገኙባቸው ሰባት ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ እቀባ፣ የእርከንና ክትር ስራዎች በማከናወን ወደ ግድቦቹ የሚገባውን ደለል አፈር የማስቀረትና የአካባቢውንም ስነ ምህዳር የሚጠብቁ ስነ ህይወታዊ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
በአካባቢው የተራቆተ 106 ሄክታር መሬትንም በመከለል ከሰው ንክኪና ከእንስሳት ልቅ ግጦሽ ነጻ በማድረግ በአጭር ጊዜ መልሶ እንዲያገግም ለማስቻል ትኩረት መሰጠቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተራቆተ መሬትን መልሰው እንዲያገግሙ በተደረገው ጥረት የከተማው የደን ሽፋን ከ9 በመቶ ወደ 12 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።
ዘንድሮም 5 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ሽፋኑን ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራው ከ8 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ የልማት ስራውም ለተከታታይ 23 ቀናት እንደሚቆይ አስረድተዋል፡፡
ያገገሙ ተፋሰሶችን በዘላቂነት ለመጠበቅና ልማቱንም ለማስቀጠል እንዲቻል ከ800 በላይ አባላት ያሏቸው 12 የተፋሰስ ህብረት ስራ ማህበራት ተቋቁመው የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ የአርሶ አደሩ የህልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከተማውንም ከጎርፍ አደጋ ለመታደግና የመጠጥ ውሃ ግድቦችንም ከደለል አፈር በመታደግ አገልግሎታቸውን ለማራዘም ያስችላል ያሉት ደግሞ የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ናቸው፡፡
አርሶ አደሩና የከተማው ነዋሪ ሰላሙን ከማረጋጋጥ ጎን ለጎን ልማቱንም እያስቀጠለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ የህዝቦች የህልውና መሰረቶች ናቸው ብለዋል፡፡
የሳይና ሳቢያ ቀበሌ አርሶ አደር ደሴ ሲሳይ እንዳሉት፤ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራው ህይወታቸውን ለመቀየር አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
በእርሻ መሬታቸው ዳርቻ ላይ እርከን በመስራት ለም አፈር እንዳይከላ ማድረጋቸውና ባገገሙ ተፋሰሶችም በሚያገኙት የመኖ ሳር በጎች በማርባት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ወይዘሮ አባቱ ክንዴ በበኩላቸው፤ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በአካባቢያቸው ደርቀው የነበሩ ምንጮች ዳግም በመጎልበታቸው ውሃ ፍለጋ ሴቶች በእግር በመጓጓዝ የሚደርስባቸውን መንገላታትና ድካም ማስቀረት እንደቻሉ ገልጸዋል።
በማስጀመሪያ ስነ-ስርአቱ የከተማውን አመራር አባላትና የአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡