ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትብብሯን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ ገለጹ።

በአፍሪካ ሕብረት ሥር የተቋቋመው የካርቱም ቀጣናዊ ተልዕኮ ማስፈጸም ማዕከል /ሮክ/ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ መክሯል። 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ፤ ኢትዮጵያ በሮክ በኩል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ረዥም ዓመት የሮክ አባል መሆኗን አስታውሰው፤ ተወካይ መድባ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከል እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም ከአባል አገራቱ ጋር፣ ከባለድርሻ አካላት እና ከፖሊስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ወንጀሉን ለመከላከል የበኩሏን አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የዛሬው መድረክም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት፣ የመረጃ ልውውጥ አድማሱን ለማስፋት፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 


 

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ከሁሉም የክልል የፖሊስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል። 

በቅርቡ በነበረው የኢንተርፖል ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሰራችው ሥራ ዕውቅና ማግኘቷንም አስታውሰዋል፡፡ 

  ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።


 

የካርቱም ቀጣናዊ ተልዕኮ ማስፈጸም ማዕከል /ሮክ/ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሀርቬ ጃሜት፤ በቀጣናው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት አባል ሀገራት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ለመዋጋት ዓይነተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የዚህ ውይይት ዋና ዓላማም ከፍትሕ አካላት ጋር የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ወንጀሉን መከላከል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡   

በአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ሮክ በአፍሪካ ሕብረት ሥር የተቋቋመ ፕሮጀክት ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 የአፍሪካ ሀገራት በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በትብብር የሚሰሩበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም