የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ መልሶ ግንባታ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ መልሶ ግንባታ ተጀመረ
አክሱም ፤ጥር 15/2016(ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ/ኤርፖርት/ መልሶ ግንባታ መጀመሩን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
የአክሱም ከተማ አስተዳደርና የማህበረሰብ ተወካዮች ትናንት አውሮፕላን ማረፊያውን ጎብኝተዋል።
የአየር መንገዱ የመሠረተ ልማት ዘርፍ ተወካይ አቶ ዓቢይ ዘበነ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት መንግሥት አውሮፕላን ማረፊያውን ወደ ሥራ ለማስገባት በመደበው በጀት የፕሮጀክቱ መልሶ ግንባታ ተጀምሯል።
መልሶ ግንባታው የተጀመረው በ290 ሚሊዮን ብር ወጪ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ የአውሮፕላን ማረፊያና ማኮብኮቢያ ሜዳውን በአዲስ መልክ መልሶ መገንባትንና የመንገደኞች ማስተናገጃ /ተርሚናል/ ጥገናና እድሳትን እንደሚያካትትም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ በአምስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ግንባታውን ከሚያከናውነው ድርጅት ጋር ውል መገባቱን ተወካዩ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን ለማከናወን ያሸነፈው የንኡድ ኮንስትራክሽን ድርጅት ተወካይ አቶ መሐመድ አብዱ የአውሮፕላን ማረፊያው መልሶ ግንባታው በተያዘለት ጊዜና በጥራት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የአክሱም ከተማ አስተዳደር፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎች የማህበረሰቡ ተወካዮች ትናንት አውሮፕላን ማረፊያውን ጎብኝተውታል።
የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ ኤርፖርት በአክሱምና በዓድዋ ከተሞች የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች የትራንስፖርት አማራጭ እንደሚሆን ተመላክቷል።