ቀጥታ፡

በምስራቅ ቦረና ዞን ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾና ቦለቄ ሰብሎች ምርት ተሰበሰበ

ነገሌ ቦረና፤ ጥር 15/2016 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ቦረና ዞን ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾና ቦለቄ ሰብሎች ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በዞኑ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያ ተፈላጊና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ሰብሎችን የማልማት ስራ መጀመሩ ተመልክቷል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቦነያ ሁቃ ዘንድሮ በዞኑ ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በገበያ በሚፈለጉ ሰብሎች ለምቷል ብለዋል፡፡ 

ምስራቅ ቦረና ቆላማ፣ ዝናብ አጠርና አልፎ አልፎ የሰብል ልማት የሚካሄድበት ሲሆን በስፋት የእንስሳት እርባታ የሚዘወተርብት አካባቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የዞኑን አርብቶ አደሮች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በገበያ የሚፈለጉ ሰብሎችን የማልማት ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡  

ዘንድሮ በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ከለሙት ሰብሎች መካከል ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾና ቦለቄ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከዞኑ 5 ወረዳዎች ከሚለሙት ከነዚሁ ሰብሎች 600 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው እስካሁን ከእቅዱ ከ602 ሺህ ኩንታል በላይ አጠቃላይ ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከዞኑ 5 ወረዳዎች 42 ሺህ 100 የሚጠጋ ኩንታል ምርት የተሰበሰበው ከሰሊጥ ሰብል ልማት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በሰብል ልማት ስራው ከ15 ሺህ በላይ የዞኑ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በዞኑ ወላቡ ሊጣ ወረዳ የኦዳ ቀበል ነዋሪ ሸህ ረመዳን መሀመድ በሰሊጥ ሰብል ልማት ከተሰማሩ ከፊል አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ 

ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን ዘንድሮ በ2 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የሰልጥ ሰብል ከ18 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውን ገልጸዋል፡፡

የሰሊጥ ሰብል ልማት በትንሽ ዝናብ በ3 ወር የሚደርስ በገበያ የሚፈለግና ለአከበቢ አየር ጸባይ የሚስማማ በመሆኑ ትኩታቸውን እንደሳበ ጠቁመዋል፡፡ 

ቦለቄ፣ አኩሪ አተርና ማሾ የመሳሰሉ ሰብሎችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ከብግብርና ባለሙያ ምክር መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡

የዚሁ አካባቢ ነዋሪ አቶ ሀሰን ሀጂ አብዱ በ2 ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ካለሙት የሰሊጥ ሰብል 25 ኩንታል ምርት ሰብስበዋል፡፡ 

በአከባቢያቸው በተለምዶ ከመስከረም እስከ ህዳር፣ ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዝያ 30 የዝናብና የዘር ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

''ከዘንድሮ ልምድ ወስጄ በመጭው መጋቢት ወር ሰሊጥ በማልማት የተሻለ ምርት የመሰበሰብ እቅድ አለኝ'' ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም