የካናዳ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማዕድንና ግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ሊሰማሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የካናዳ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማዕድንና ግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ሊሰማሩ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥር 15/2016 (ኢዜአ)፦ በማዕድንና ግብርና ማቀነባበሪያ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የካናዳ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በሂደት ላይ መሆናቸውን በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ተናገሩ።
አምባሳደር ፍጹም አረጋ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም በማዕድን ልማትና ግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ካናዳ በማዕድን ልማት ከፍተኛ ልምድና ብቃት እንዲሁም አለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው ግዙፍ ኩባንያዎች የሚገኙባት አገር እንደሆነች ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በአስር አመት የልማት መሪ እቅዷ ውስጥ ትኩረት ከሰጠቻቸው ዘርፎች አንዱ ማዕድን በመሆኑ በወርቅና ሌሎች ዘርፎች ያለውን እምቅ ሃብት በማስተዋወቅ ባለሃብቶችን የመሳብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም "አላይድ ጎልድ" የተባለ ግዙፍ የካናዳ ወርቅ አምራች ኩባንያ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ፈሰስ የሚደረግበት ፕሮጀክት ይፋ በማድረግ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ይጠበቃል ብለዋል።
በተመሳሳይ በፖታሽ ዘርፍም ኩባንያዎች እንዲሰማሩ የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አምባሳደር ፍጹም ገልጸዋል።
በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ አንድ መቶ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ነድፎ የመጣ የካናዳ ኩባንያ መኖሩን አብራርተዋል።
እንደ አምባሳደር ፍጹም ገለጻ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከፍተኛ አቅም ካላቸው ስድስት ኩባንያዎች ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ቀድመው የነበሩና በአዲስ መልክ እየለሙ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችንና መሰረተ ልማቶችን የማስተዋወቅ ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ አምባሳደር ፍጹም አስታውቀዋል።