የህብረት ስራ ማህበራትን በፋይናንስ የሚደግፍ ባንክ ሊኖር ይገባል- የህብረት ስራ ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ማህበራትን በፋይናንስ የሚደግፍ ባንክ ሊኖር ይገባል- የህብረት ስራ ማህበራት
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2016(ኢዜአ)፦ የህብረት ስራ ማህበራትን አቅምና ገበያ የማረጋጋት ሚና ለማሳደግ ስራቸውን የሚደግፍ የፋይናንስ ተቋም ሊኖር እንደሚገባ የህብረት ስራ ማህበራት ኃላፊዎች ገለፁ።
በኢትዮጵያ የሕብረት ስራ ማህበራትን በዘመናዊ መልኩ ማደራጀት ከተጀመረ ከ 60 ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡
ማህበራቱ አምራቹንና ሸማቹን ህብረተሰብ በምርትና አገልግሎት በማስተሳሰር ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋና በተፈለገው ጊዜና ቦታ ለማቅረብ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን በተያዘው አመት የህብረት ስራ ማህበራትን በፋይናንስ የሚደግፍ ባንክ እንዲሁም ማህበራቱን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወክል ሊግ ለመመስረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 985/2009 መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት ፣ የኅብረት ሥራ ማህበራት ዩኒዬኖችና ፌዴሬሽኖች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚወክላቸውን ሊግ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ይደነግጋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የህብረት ስራ ማህበራት ኃላፊዎች እንዳሉት ማህበራቱ በጋራ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት አደረጃጀት ሊኖር ይገባል።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የንጋት ዩኒየን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ ተክሌ ዩኒየኑ በ15 መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት በ2003 ዓ.ም የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒየኑ የተለያዩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለአባል መሰረታዊ ማህበራት በማከፋፈል ገበያን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተመረጡ የግብርና ምርቶች መግዣ የሚውል 50 ሚሊየን ብር በተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ መሰጠቱ እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል።
ሆኖም ገበያን ለማረጋጋት የሚወጡትን ሚና ለማጎልበት ተጨማሪ ፋይናንስ የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህንኑ የሚደግፍ የህብረት ስራ ባንክ ቢመሰረት ስራቸውን ተደራሽ ማድረግ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ከፋይናንስ ተደራሽነት ባለፈ የህብረት ስራ ማህበራትን ችግር የሚፈታ የህብረት ስራ ማህበራት ሊግ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የአሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተርና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ይልማ በበኩላቸው ማህበሩ ከ 11 ዓመት በፊት በ 20 አባላትና በ 9 ሺህ ብር ካፒታል መመስረቱን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የአባላቱ ቁጥር ከ 7 ሺህ በላይ እንደደረሰና ካፒታሉም ግማሽ ቢሊየን ብር መጠጋቱን በመጥቀስ የህብረት ስራ ማህበራት አባላትን ተጠቃሚነት ለማሳደግም የህብረት ስራ ባንክ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አገር ማህበራት ልምድ፣ ተሞክሮ ፣ስልጠናና የአቅም ግንባታ ስራዎችን የሚያከናውኑበት ፌዴሬሽንና ሊግ የመሰሉ ተቋማት በአገሪቱ መጠናከር አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን የህብረት ስራ ማህበራት ያለባቸውን የአደረጃጀት፣ የአሰራር፣ በባለሙያ ያለመደራጀትና የፋይናንስ ችግር ለማስተካከል የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጿል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ እንዳሉት በኢትዮጵያ በርካታ የህብረት ስራ ማህበራት ቢኖሩም ባላቸው ቁጥር ልክ የገበያ ድርሻና የዋጋ ማረጋጋት ተግባር ላይ እየተሳተፉ አይደለም።
በአገሪቱ የሚገኙ መሰረታዊ ማህበራት ጤናማ የሆነ አሰራር እንዲኖራቸው የሚያስችል ኦዲት ለማከናወን የሚረዳ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግስት የተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ የፋይናንስ ችግራቸውን ለመፍታት እየሰራ ቢሆንም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ፋይናንስ እንዲያገኙ ለማስቻል የራሳቸው የፋይናንስ ተቋም እንደሚያስፈልጋቸው አስረድተዋል።
በተለያዩ አገራት የህብረት ስራ ማህበራትን በፋይናንስ የሚደግፍ የህብረት ስራ ማህበራት ባንክ እንዳለ አንስተው በኢትዮጵያም መሰል ባንክ እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ማህበራቱን በፌዴራል ደረጃ የሚወክል ሊግ ለመመስረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
በአገሪቱ 110 ሺህ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት፣ 403 ዩኒየኖችና 5 ፌዴሬሽኖች መኖራቸውን ጠቅሰው ማህበራቱ አሁን ላይ ካፒታላቸው ወደ 59 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ እነዚህ ማህበራት ከገበያ ተቀባይነት በመውጣት ገበያ ሰጪ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚረዱ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡