የሉሲ መገኘት ለሳይንስ ዘርፉ የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መሆኗን ያመላከተ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ መገኘት ለሳይንስ ዘርፉ የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መሆኗን ያመላከተ መሆኑ ተጠቆመ
ሰመራ፤ ጥር 15/2016 (ኢዜአ)፦ የሉሲ መገኘት ለሳይንስ ዘርፉ የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መሆኗን ያመላከተ መሆኑ ተጠቆመ።
የዛሬ 50 ዓመት (ሉሲ)ድንቅነሽን በምርምር ባገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰን የተመራ የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር ቅሪተ አካል ተመራማሪ ቡድን ሰመራ ገብቷል።
ቡድኑ ሱልጣን አሊሚራህ ሀምፍሬ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አመራር አባላት፣ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ተማሪዎች እና የክልሉ የባህል ቡድን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሉሲ(ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል እ.ኤ.አ በ1974 በአፋር ክልል አዋሽ ሸለቆ አደአር ወረዳ በሚገኘው ሀዳር በሚባል አካባቢ በተመራማሪዎች መገኘቷ ይታወሳል።
ቅሪተ አካሉ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት እንደሆናት ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል።
በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር መገኛ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዮሐንስ ሃይለስላሴ፤ የሉሲ መገኘት ለሳይንስ ዘርፉ የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት "ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መሆኗን ያመላከተ ነው" ብለዋል።
የምርምር ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ሉሲ(ድንቅነሽ) የተገኘችበት 50ኛ ዓመት መቃረቡን ታሳቢ በማድረግና ኢንስቲትዩቱ በተለይም ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቀጣይነት ለመስራት እንዲችል ምክክር ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ሉሲ(ድንቅነሽ) የተገኘችበት ሀዳር አካባቢም ቡድኑ ጉብኝት እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን በሰመራ ዩኒቨርሲቲም ከዘርፉ ምሁራን ጋር እንደሚመክር ታውቋል።
የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር የቅሪተ አካል ተመራማሪ ቡድኑን በተቀበሉበት ወቅት፤ በፕሮፌሰሩ ጥናትና ምርምር ግኝት ኢትዮጵያ የዓለም የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ይፋ ሆኗል ብለዋል።
የተመራማሪ ቡድኑ ወደ አካባቢው መምጣት ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ የቱሪዝም መነቃቃት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።