ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ለማልማትና ተጠቃሚነት ለመጨመር ብዝሃ አማራጮችን በመመልከት ዕድሉን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ድሬዳዋ፤ ጥር 15/ 2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የባህር በር ለማልማትና ተጠቃሚነት ለመጨመር ሌሎች የጎረቤት ሀገራት አማራጮችን በመመልከት ዕድሉን ማስፋት እንደሚያስፈልግ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ፣ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የቀጣናውን የባህር በር እና የወደብ አገልግሎት አማራጭ የሚያሰፋ ታሪካዊ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ በቅርቡ በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ይታወሳል።

ይህን የሰጥቶ መቀበል መርህና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጎለብተውን ስምምነት ደግሞ የዘርፉ ምሁራን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና በአካባቢው ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው። 

መሰል የመግባቢያ ስምምነቶች ደግሞ የባህር በርና የወደብ ልማትና ተጠቃሚነት አማራጮችን ከማስፋቱም በላይ የቀጣናውን የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናከር መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ለማልማት እና የወደብ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ስምምነት ጉዳይ በአንድ አገር ላይ ብቻ ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋርም ለመስማማት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

በዩኒቨርስቲው የፖለቲካ ሣይንስና ዓለምአቀፍ ትምህርት ክፍል መምህርት መቅደስ ካሣሁን እንዳሉት ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት እንደ መነሻ አድርጋ "ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋርም ስምምነቱን ማስፋት ይገባታል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችውን ጥረት ማሳካት ማለት የአገርን ሁለንተናዊ ዕድገት ከማፋጠንና የዜጎችን ኑሮ በመሠረታዊነት ከመለወጥ ባሻገር ቀጣናዊ ትስስሩንም እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

ሌላው በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሣይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ናኒ ደበሌ በበኩላቸው፤ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የዓለም የእይታ ትኩረት የሳበና የብዙሃን ተቃርኖ መገለጫ ቀጣና እየሆነ የመጣ አካባቢ ነው።

የኢትዮጵያ የባህር በርና የወደብ የባለቤትነትና ስምምነት ጥያቄም ሆነ አልምቶ የመጠቀሙ ሂደት "በአንድ ሀገር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆን የለበትም" ብለዋል። 

ይኸም የወደብ አማራጭን ከማስፋቱም በላይ የቀጣናውን ዲፒሎማሲያዊ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርንም ያጠናክራል፤ በዘርፉ የሚመጡ ተግዳሮቶችንም የመቀነስ እድል እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በተለያየ ጊዜ በተፈጠሩ ፖለቲካዊ ስህተቶች ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ዓለምሰገድ ደጀኔ ናቸው።


 

ለወደፊቱም በዘርፉ የሚደረጉ መሰል የስምምነት ሂደቶች ያለፉትን ስህተቶች በማይደግም አኳኋን መሆን እንደሚገባቸው በማውሳት።

 “ወደብ ለአንድ አገር ጉሮሮ ነው” የሚሉት መምህር ዓለምሰገድ፤ ኢትዮጵያም በቅርቧ ካሉ የወደብና የባህር በር ባለቤት ሀገራት ሁሉ ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ስምምነት ፈጥራና አልምታ የመጠቀም አማራጭ እንዳላት የዓለም ህግ እንደሚፈቅድላት ያረጋግጣሉ።

መሰል የባህር በርና የወደብ ባለቤትነት የመግባቢያ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የጋራ እድገትና ውህደት ለመፍጠር የሚያስችል የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ መሆኑንም ምሁራኑ ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም