ኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ቀድማ ለማሳካት እየሰራች ነው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ቀድማ ለማሳካት እየሰራች ነው - ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ2030 የእብድ ውሻ በሽታን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ቀድማ ለማሳካት በትኩረት እየሰራች መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
አዲስ የተገነባው የውሻ እብደት በሽታ መመርመሪያ ላቦራቶሪ በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
በዚህ ወቅት ዶክተር ፍቅሩ እንደገለጹት አዲሱ የእብድ ውሻ በሽታ መመርመሪያ ላቦራቶሪ የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል፡፡
በኢትዮጵያ የውሻ እብደት በሽታ በሕይወትና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከሚያደርሱ የእንስሳት በሽታዎች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑንም ዶክተር ፍቅሩ አክለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህን በሽታ በጋራ በመከላከል እ.አ.አ. በ2030 በሽታውን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ቀድማ እንድታሳካ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ሩፋዬል አዲሱ ላቦራቶሪ የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ላቦራቶሪው በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ላሉ ሀገራትም ጭምር አገልግሎት እንደሚሰጥ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ላቦራቶሪው ወደ ስራ እንዲገባ ድጋፍ ላደረጉ አካላት እና ለተቋሙ ባለሙያዎች የእውቀት ሽግግር ስልጠና ለሰጠው የደቡብ አፍሪካ የእንስሳት ጤና ኢንስትቲዩት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቀጣናው የእንስሳት በሽታ መቆጣጠር ድጋፍ ሰጪ(ARC) ኢንስቲትዩት ማኔጀር ዶክተር ሚሼክ ሙሉምባ ተቋማችው በተለያዩ የእንስሳት በሽታ አይነቶች መከላከል ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በላቦራቶሪው ምርመራ የሚገኙ የተለያዩ የእንስሳት በሽታዎች ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡