ለሽብር ወንጀል ይውል የነበረ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
ለሽብር ወንጀል ይውል የነበረ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14/2016 (ኢዜአ) ለሽብር ወንጀል ይውል የነበረ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
እንደ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መረጃ መነሻቸውን ከአማራ ክልል በማድረግ አዲስ አበባ ከተማን አልፎ በቱሉ ዲምቱ የፍተሻ ጣቢያ ለማለፍ የሞከረው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ2-አ/አ 13092 cobra 1 መቶ 6 ኢኮልና የቱርክ ሽጉጦች፣ 26 ሺህ 624 ከመሠል ጥይቶች፣ 60 የክላሽንኮቭ ጥይቶችን እንደጫነ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ ክትትልና ፍተሻ ሁለት ተጠርጣሪዎች ከሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎቹ ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በቱሉ ዲምቱ የፍተሻ ጣቢያ የተያዘውን ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ መነሻ በማድረግና ምርመራውን በማስፋት ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ አውጥቶ በየካ ክፍለ ከተማ ኮቶቤ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቤተል አካባቢ በሚገኙ የተጠርጠሪዎች መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ ኮድ 2- አ/አ 67251 Dx ተሽከርካሪ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎቹን እንደጫነ መያዙ የተገለፀ ሲሆን በተመሳሳይ ወንጀል መፈፀሚያ ይገለገሉበታል ተብሎ የተጠረጠረ ኮድ3-ዲሬ 06614 TOYOTA PICKUP ዳብል ገቢና ተሽከርካሪም አብሮ መያዙ ታውቋል።
እንደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ለማወቅ እንደተቻለው እነዚህ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በአዲስ አበባ እና አካባቢው ላይ የጥፋት ተልዕኮ ለመፈፀም ታስቦ ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ እና ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎቹ በፀረ-ሰላም ኃይሎች እጅ ቢገቡ ኖሮ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችሉ ታውቋል።
በፍተሻ ጣቢያው ከአሁን በፊትም የተለያዩ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች እየተያዙ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን ለመቆጣጠር የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡