ትውልዱ ከአድዋ ጀግኖች የተረከባትን ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞች በውል በመለየት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መትጋት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ ከአድዋ ጀግኖች የተረከባትን ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞች በውል በመለየት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መትጋት አለበት
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2016(ኢዜአ)፦ ትውልዱ ከአድዋ ጀግኖች የተረከባትን ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞች በውል በመለየት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ መትጋት እንዳለበት ተገለጸ።
"አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ የሰላም ሚኒስቴር ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሙክታር ጠይብ፤ አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታና ሀገራዊ እሴቶች በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።
የሀገራትን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ተሞክሮና ኢትዮጵያ በአድዋ ድል ራሷን ያስከበረችበትን መንገድ በጽሑፋቸው በንፅፅር አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት የመንግሥት ታሪክ ያላት፣ ብዝኃ ማንነት ያለው ሕዝብ የሚኖርባት፣ የሰው ልጅና የሥልጣኔ መገኛ ምድረ-ቀደምት መሆኗን ጠቅሰው፤ ብዝኃነትን ማስተናገድና የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበር የጋራ የጀግንነት መገለጫዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርጉ የሀገር ጥቅሞች መኖራቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ቀጣናዊና ታሪካዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትውልዱ ከአድዋ ጀግኖች የተረከባትን ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞች በውል መለየት እንዳለበትም አመላክተዋል።
የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ዘመን ተሻጋሪ የተቋም ግንባታ፣ ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ በምግብ ራስን መቻል፣ የሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ ሀገራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ተልዕኮውን ለመወጣትም ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካውያንና መላው ጥቁሮች የሚኮሩበት መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ያለው ትውልድ ከቀደምቶቹ ፍቅርንና አንድነትን መማር አለበት ብለዋል።
አድዋ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ አካል መሆኑን አንስተው፤ በዚህ ዘመንም ዜጎች ከራስ ፍላጎት ያለፈ ዕይታን፣ አብሮነትን፣ ማጠናከር እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ሀገራዊ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን በማዳበር የውጭ ኃይሎችን ሀገር የማዳከም ሴራን ማክሸፍ የዘመኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መሐመድ ዑስማን፤ ሀገር የሚገነባው በትውልዶች መካከል ባለ ጠንካራ የስነ-ልቦና ትስስር እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ታሪካዊ ድሎችን ለሀገር ግንባታ የማዋል፣ በሀሳብና በእውቀት ልዕልና የሚያምን ትውልድ የመገንባት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የሀገርና የሕዝብ ህልውናን ማስጠበቅ የሚቻለው በእውቀትና በቴክኖሎጂ ልህቀት መሆኑንም ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ፤ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በከፈሉት ዋጋ ከብረት የጠነከረ ትስስር እንዳላቸው ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አብሮነትን ለማላላት የሚሞክሩ አካላት ሀገርን የማዳከም ዓላማ ይዘው መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም የሀገርን ሰላም ለማፅናትና እድገትን ለማረጋገጥ ሁሉም በኃላፊነት መንቀሳቀስን ከፋፋይ ትርክቶችን ማስወገድ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በእርግጥም የነገዋን ኢትዮጵያ የሚገነባ ትውልድ የሚፈልቅባቸው ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ከእነክብሯ የተረከቧትን ሀገር ለማስቀጠል የሕዝቡን የአብሮነት እሴት ማጎልበት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት መገንባትም የዚህ ዘመን ትውልድ አደራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማሕዲ፤ የአድዋ ድል ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የፅናትና የጀግንነት እሴትን ለትውልዱ ያወረሰ ዘመን ተሻጋሪ ገድል ነው ብለዋል።
ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የጥቁሮች የኩራት ምንጭ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ፈትሂ፤ ከአድዋ በመማር ሕብረ- ብሔራዊነትን ማጠናከርና ችግሮችን በተባበረ አቅም መሻገር ይገባል ነው ያሉት።
ወራሪን ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን ባወረሱን ጀግንነት ድህነትን ማስወገድ፣ ሀገርን በመስዋዕትነት ማስቀጠል፣ እንዲሁም ለውጫዊና ውስጣዊ ጫና የማይበገር መሆን ይጠበቅብናል ነው ያሉት።