ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምጣኔ ሃብት ብልጽግና ለማምጣት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምጣኔ ሃብት ብልጽግና ለማምጣት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምጣኔ ሃብት ብልጽግና ለማምጣት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ መቀጠሏን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክተር አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ተናገሩ።
ጀነራል ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በአፍሪካ እንዲሁም በአለም የዲፕሎማሲ መድረክ ስትጫወት የነበረው ጠንካራ ሚና ጸንቶ መቀጠሉን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት አገራት በመስጠት ወደ አህጉር በመቀጠል ወደ አለም እየሰፋ የሚሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ የነጻነት ትግል በፋና ወጊነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጎረቤት አገራትን እና መላውን አፍሪካ በማስተባበር የምጣኔ ሃብት ብልጽግናን ለማምጣት እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎት ጎረቤት አገራትን በማስተባበር መልካም የሆነ ድንበር ዘለል ግንኙነት ማምጣት፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ገንዘብና ካፒታል በነጻነት የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ መፍጠር ነው።
አፍሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊነትን በተላበሰ መልኩ ሰጥታ የምትቀበል እንድትሆን ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
የአፍሪካ ነጻነትና ሉአላዊነት እንዲከበር የተለያዩ ተቋማትን በመመስረት የተጫወተችውን ግንባር ቀደም ሚና የምጣኔ ሃብት ብልጽግና ለማምጣት እየተጠቀመችበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የአፍሪካ አገራት በምጣኔ ሃብት፣ በመሰረተ ልማትና በንግድ ያላቸውን ትብብር የበለጠ እንዲያጠናክሩ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለውን ሚና አስረድተዋል።
የመሰረተ ልማት ትስስርን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያንን ከተቀረው አለም ጋር በማገናኘት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የንግድ ትስስርን እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና የሚኖረውን የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
በአህጉሪቷ በህዝብ ቁጥሯ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠችውና ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሰላም፣ በምጣኔ ሃብት እድገትና በብልጽግና ዙሪያ ያላት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የመሪነት ሚና የሚከተሉ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በመኖራቸው ኃላፊነቷን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ነው አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ያብራሩት።
ኢትዮጵያ በውስጥ ሆነ በውጭ መካከለኛና አማካኝ አቋም በመያዝ ራሷን ፣ጎረቤት አገሮችንና አህጉሪቷን በጋራ የማልማት ጽኑ ፍላጎቷ እንዳላትም አረጋግጠዋል።