ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የላቀ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የላቀ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2016(ኢዜአ)፦ ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የላቀ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም ምስረታ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩም በዳያስፖራ ተሳትፎ ሂደት የገጠሙ ፈተናዎች፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ባዘጋጀው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሌንሳ መኮንን፣ ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የወከሉ አምባሳደሮችን ጨምሮ ምሁራንና ዳያስፖራ አባላት ተገኝተዋል።
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረሙ ከምሁራን፣ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ጉዳይ የነቃ ተሳትፎ ያላቸው ዜጎችን በአባልነት ያቀፈ ነው።
ፎረሙ ከ25 አገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያን የተካተቱበት ሲሆን ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ጉዳይ በምን መልኩ ይሳተፍ?፣ የዳያስፖራው ለማሳተፍ ሊመቻቹ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግሥት ጋር በመመካከር የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ መሆኑም ተመላክቷል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በልማት ተሳትፎ፣ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍና በሰብአዊ ድጋፎች አበረታች ተሳትፎ እያደረጉ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የላቀ ተሳፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
"ኢትዮጵያን ወደ ዕድገት ጎዳና የሚያደርሱ ጅምሮች ስላሉ ከዳር ለማድረስ የዳስፖራ አባላት ተሳትፎ ሲታከልበት በመሆኑ ኑ አገራችንን በጋራ እንገንባ" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ የሚሰራ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም መቋቋሙ ትልቅ እርምጃ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ምስጋኑ ፎረሙ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣ በንቅናቄ መልክ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማሪያም፤ የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተኑ ችግሮችን ለመታገል የዳያስፖራው አንድነት ያስፈልጋል ብለዋል።
"የሀገር ጉዳይ ከፓርቲ እና ከመንግሥት ጋር የሚያያዝ አይደለም፤ በሀገራችን ብሄራዊ ጥቅም ላይ የሁላችንም አንድነትና ተሳትፎ ሊኖር ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።
በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የሚሰራ "አባይድ" የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ተዋበች ቢሻው፤ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውንን እውቀት ለአገር ልማትና እድገት ለማዋል ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በመሆኑም መንግሥት የዳያስፖራውን እውቀት በአግባቡ ለመጠቀም ኢንቨስት ማድረግ አለበት፤ በትኩረትም ሊሰራበት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።