ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቀን የጋራ ነጻ የጉብኝት መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቀን የጋራ ነጻ የጉብኝት መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ለመጡ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቀን የጋራ ነጻ የጉብኝት መርኃ ግብር ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ለገቡ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መርኃ ግብሮችን በማዘጋጀት ሀገራቸውን በስፋት እንዲያውቁ እየተደረገ ነው።
በዚህም አየር መንገዱ ያዘጋጀውን የጉብኝት መርኃ ግብር አስመልክቶ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለማ ያዴቻ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አገራቸው እየመጡ ላሉ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ትኬት የጭነትና በስካይ ላይት ሆቴሎች ቆይታ ለሚያደርጉ እንግዶች ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚደረስ ቅናሽ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም እንግዶቹ በአገር ውስጥ የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው አንስተዋል።
በቅርቡ ከ100 በላይ ለሚሆኑ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቀን የጋራ ነጻ የጉብኝት መርኃ ግብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ጉብኝቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን እስካሁን 70 የሚሆኑ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን በጉብኝቱ ለመካፈል መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የጉብኝት መርኃ ግብሩ የአገራዊ ጥሪውን ዓላማ ለማሳካት የሚያግዝ ከመሆኑ ባሻገር ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ስለ አገራቸው ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከባህላቸው ጋር እንዲተዋወቁና አገራቸውን እንዲያውቁ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።