ቀጥታ፡

በአጣብቂኝ ውስጥ ያለው የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን ማሸነፍን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ምሽት ላይ ከጋምቢያ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2016(ኢዜአ)፦በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአህጉሪቷ እግር ኳስ ስኬታማ ታሪክ ያላቸው አገራት በወረቀት ላይ የተሰጣቸውን ያህል ግምት በመጫወቻ ሜዳው ላይ እያሳዩ አይገኙም።

የነዚህ አገራት የተጠበቁትን ያህል ያለመሆን የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ አጓጊ አድርጎታል።

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ ከማይገኙ አገራት መካከል የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን አንዱ ነው።

የማይበገሩት አንበሶች የሚል ተቀጽላ ስም ያለው ብሔራዊ ቡድኑ እ.አ.አ በ1984፣1988፣2000፣2002 እና 2017 የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ከግብጽ በመቀጠል አህጉራዊ ክብሩን ለበርካታ ጊዜ መጎናጸፍ ችሏል።

ካሜሮን ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳቸው እ.አ.አ በ2017 ጋቦን ባዘጋጀችው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በአህጉሪቷ እግር ኳስ ውስጥ የነበራት ስኬትና አይበገሬነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየራቃት ይገኛል።

እ.አ.አ በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ሰባት የነበረችው ካሜሮን ከምድቧ ማለፍ አልቻለችም።

የማይበገሩት አንበሶች በዓለም ዋንጫው ያሳዩት ብቃት ካሜሮናውያንን ያስደሰተ አልነበረም።

በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሶስት የምትገኘው ካሜሮን በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከጊኒ ጋር 1 ለ 1 የተለያየች ሲሆን በሁለተኛ የምድብ ጨዋታዋ በወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ሴኔጋል 3 ለ 1 ተረታለች።

ዛሬ ወደ ጥሎ ማለፉ ለመግባት ከጋምቢያ ጋር ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ በዴ ላ ፓክስ ስታዲየም ወሳኝ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

ውጤቶቹን ተከትሎም ካሜሮን በ1 ነጥብና በ2 የግብ እዳ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ማሸነፍ ብቸኛዋ አማራጭ የሆነው ካሜሮን ጋምቢያን ከረታች ከሌሎች ምድቦች ጋር ታይቶ ጥሩ ሶስተኛ ሆኖ የማለፍ እድል ይኖራታል።

ጋምቢያን ከሁለት ጎል በላይ አሸነፉ ሴኔጋል ጊኒን ከአንድ ጎል ልዩነት በላይ ከረታች ሁለተኛ ሆኖ የማለፍ እድልም ይኖራታል።

በሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደችው ጋምቢያ የዛሬው ጨዋታ ከመርሐ ግብር ማሟያነት የዘለለ ትርጉም የለውም።

የ43 ዓመቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ የሁለቱን ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በዚሁም ምድብ በተመሳሳይ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በቻርልስ ኮናን ባኒ ስታዲየም አስቀድሞ ወደ ጥሎ ማለፉ የገባችው ሴኔጋል ከጊኒ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።

ሴኔጋል የምድቧን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ስድስት ነጥብ የያዘች ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ምድቡን በመሪነት እንድታጠናቅቅ ያደርጋታል።

ከሁለት ጨዋታ አራት ነጥብ የሰበሰበችው ጊኒ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ የሚያስገባትን ትኬት መቁረጥ የሚያስችላት ሲሆን ብትሸነፍም ያላት አራት ነጥብ ጥሩ ሶስተኛ ሆና የመጨረስ እድል ይሰጣታል።

በተያያዘም በምድብ አራት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ አልጄሪያ በዴ ላ ፓክስ ስታዲየም ከምሽቱ 5 ሰዓት ከሞሪታኒያ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።

የበረሃ ቀበሮዎቹ በምድባቸው እስከ አሁን ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ከአንጎላ 1 ለ 1 እንዲሁም ከቡርኪናፋሶ 2 ለ 2 በሆነ የአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ውጤቶችን ተከትሎ አልጄሪያ በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አልጄሪያ ማሸነፍ ከምድቧ ሁለተኛ ሆና በቀጥታ የሚያሳልፋት ሲሆን አቻ ብትወጣም ቡርኪናፋሶና አንጎላ ተከትላ ምርጥ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድል አላት።

ሞሪኒታኒያ በምድቡ ያደረጋቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች መሸነፏን ተከትሎ ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏ እጅጉን የተመናመነ ነው።

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ከምሽቱ 5 ሰዓት አንጎላ ከቡርኪናፋሶ በቻርልስ ኮናን ቦኒ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አንጎላና ቡርኪናፋሶ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የጨዋታው አሸናፊ አገር በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገባ ሲሆን ተሸናፊው ቡድን ሁለተኛ ወይም ጥሩ ሶስተኛ ሆኖ የማለፍ እድል አለው።

አቻ መውጣትም ሁለቱን አገራት ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያሳልፍ ይችላል።

የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ነገ ይጠናቀቃሉ።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም