ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2016 (ኢዜአ)፦ ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በዜጎች የነቃ ተሳትፎ ከሚገነቡ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች አንዱና ቀዳሚው ነው።
እንደ አገር ሰንደቅ የሚቆጠረው ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ኢትዮጵያውያን የግድቡ መሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በገንዘባቸው፣በእውቀታቸው እንዲሁም በጉልበታቸው የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህን ተከትሎ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ድጋፎችን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር ጽህፈት ቤቱ ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከህብረተሰቡ ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ከህብረተሰቡ 625 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ503 ሚሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
ገቢው ከተሰበሰበባቸው መንገዶች ውስጥ ከሀገር ውስጥ የቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከዲያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከፒን ሽያጭ እና 8100 ኤ በአጭር የሞባይል የጽሁፍ መልእክት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ በክልሎች የሚደረገው የድጋፍ ስራ ወጥ አለመሆን ግቡን ለማሳካት ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል ።
ኢትዮጵያ የወጠነችውን የልማት ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም ለግድቡ ግንባታ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ከጽህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።