ቀጥታ፡

ከቆሬ እስከ አቢጃን

የተወለደው በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቆሬ የሚባለው አካባቢ ነው። ያደገው ደግሞ መገናኛ።

በልጅነቱ ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅርና ስሜት የነበረው ሲሆን በሰፈር ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር ኳስ በመጫወት አፍላነቱን አሳልፏል።

የቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ወክሎ የተጫወተ ሲሆን በአማካይ ስፍራ ላይ መጫወት ምርጫው ነበር።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታዎችን መከታተል ያስደስተው እንደነበርም ይናገራል፡፡

በእግር ኳስ ተመልካችነቱ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች የነበረውን የካሳዬ አራጌ አጨዋወት መመልከት እንደሚያስደስተው ከዚህ ቀደም ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋር በነበሩት ቃለ መጠይቆች ገልጿል።

ታሪኩን የምናወጋችሁ ግለሰብ የእግር ኳስ ተጫዋች ሳይሆን ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ነው።

ወደ ዳኝነት ዓለም መንደርደሪያ 

በእግር ኳስ ፍቅሩ  ባደገበት መገናኛ አካባቢ በሰፈር ውስጥ የሚካሄዱ ጨዋታዎችን በዳኝነት በመምራት አንገቱን በትንሹ ወደ ሙያው ለማስገባት ችሏል።

ይህንን የተመለከተው ኤልያስ እንዳለ የተባለ ግለሰብ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወደ ዳኝነት ሙያ እንዲገባ ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳደረገለት ይናገራል።

ኤልያስ የተለያዩ የስፖርት ሁነቶችን በማዘጋጀት ይታወቅ ስለነበር በወቅቱ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ወደ አካባቢው በማምጣት ለታዳጊ ተጫዋቾች ተሞክሮአቸውን እንዲያካፍሉ ያደረግ እንደነበር ይገልጻል። 

ይህ ግለሰብ ባምላክ በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስልጠና እንዲያገኝና የፕሮፌሽናልነት ጉዞውን እንዲጀምር በር ከፍቶለታል።

ባምላክ በመገናኛ አካባቢ የሚደረጉ የሰፈር ውስጥ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ከመምራት ተነስቶ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ጨዋታዎች በመምራት ባሳየው ብቃት አድናቆት የሚቸረው ዓለም አቀፍ ዳኛ ለመሆን በቅቷል።

የቀድሞዎቹን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለመላክ ተሰማና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንፈ ይልማን አርዓያ በማድረግ ለዚህ ደረጃ መብቃቱን ይናገራል። 

ባምላክ ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ  

ባምላክ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የደርቢ ጨዋታዎችን ጨምሮ በርካታ ወሳኝ ጨዋታዎችን ማጫወት ችሏል። 

እንደ ባምላክ ገለጻ ፤ በአገር ውስጥ ሊግ የሚካሄዱ ጨዋታዎችን መምራት ለአንድ ኢትዮጵያዊ ዳኛ ክህሎቱና ብቃቱን ለማሳደግ ወሳኝ አስተዋጽኦ አለው።

አሁን ለደረሰበት ደረጃም ሆነ በቀጣይ በዳኝነት ለሚኖረው ሕይወቱ የአገር ውስጥ ሊግ ጨዋታዎችን መምራት ለዳኝነት ብቃቱ መሻሻል ቁልፍ ነው ብሎ ያምናል።

ከ21 ዓመት በፊት ዳኝነት የጀመረው ባምላክ ተሰማ እ.አ.አ በ2009 በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር የዓለም አቀፍ ዳኝነት ባጅ አግኝቷል።

በዚህም በ2019 /2020 የውድድር አመት ወደ ቱኒዚያ በመጓዝ የአገር ወስጥ ሊግ ጨዋታዎችን የመምራት ዕድል አግኝቷል፡፡

የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመራው እ.አ.አ በ2010 በሶማሊያና ጅቡቲ መካከል የተደረገውን ጨዋታ ነው።

ባምላክ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ውድድሮች በመዳኘት የረጅም ጊዜ ልምድ አካብቷል።

እ.አ.አ በ2018 በሩሲያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ውድድሩን እንዲያጫውት ቢመረጥም በውድድሩ በዋና ዳኝነት የመራው ጨዋታ አልነበረም።

ይሁንና ባምላክ እ.አ.አ 1970 ሜክሲኮ ባስተናገደችው ዘጠነኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በዳኝነት ኢትዮጵያን ከወከሉት ስዩም ታረቀኝ ቀጥሎ ኢትዮጵያን በዓለም ዋንጫው የወከለ ሁለተኛ ዳኛ መሆን ችሏል።

ባምላክ በ21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከተመረጡ ስድስት አፍሪካውያን ዳኞች መካከል አንዱ ነበር።

ከአራት ዓመት በፊት በጃፓን ቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በእግር ኳስ ውድድር እንዲያጫውቱ ከመረጣቸው ዋና ዳኞች መካከል ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ እንዱ ሆኖ መመረጡ ይታወሳል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በዋና ዳኝነት ሲያጫውት 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

ባምላክ እ.አ.አ በ2018 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተካሄደው የፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜ የሜክሲኮው ቺቫስ ጓድላሃራ የጃፓኑን ካሺማ አንትለርስን 3 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያለፈበትን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት መርቷል።

ፊፋ በተለያየ የእድሜ እርከን በሚያካሂዳቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም በዋና ዳኝነት አገልግሏል።

ባምላክ በአፍሪካ ዋንጫ 

ወደ አፍሪካ ስንመጣም በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) እና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስተናጋጅነት በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ብቃቱን በሚገባ አሳይቷል።

እ.አ.አ በ2017 በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በግብጹ አልአሀሊና በሞሮኮው ዋይዳድካዛብላንካ መካከል የተደረገውን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ የመራበት ብቃት ከብዙዎች አድናቆት አስችሮታል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ "ጨዋታውን በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኜ ነው በብቃት የመራሁት"ሲልም ይገልጸዋል።

እ.አ.አ በ2023 በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አልአህሊ በሜዳው የሞሮኮውን ዋይዳድካዛብላንካን 2 ለ 1 በድምር ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ለ11ኛ ጊዜ የውድድሩን ዋንጫ ያነሳበትን የመልስ ጨዋታም በብቃት መርቶታል። 

በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገው እ.አ.አ በ2015 በኢኳቶሪያልጊኒ አስተናጋጅነት በተካሄደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።

በምድብ አራት ካሜሮንና ጊኒ አንድ አቻ የተለያዩበት ጨዋታ በአፍሪካ ዋንጫ በዋና ዳኝነት የመራው የመጀመሪያ ጨዋታው ነው።

እ.አ.አ በ2017 በጋቦን አስተናጋጅነት በተካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጊኒቢሳው ከቡርኪናፋሶ እና አልጄሪያ ከዚምባቡዌ ጋር ያደረጓቸውን የምድብ ጨዋታዎች በዋና ዳኝነት መርተዋል።

በግብጽ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2019 በተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባምላክ ሶስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎውን አድርጓል።

ቱኒዚያ ከአንጎላ እና ካሜሮን ከጋና ያደረጓቸውን የምድብ ጨዋታዎች ከመምራት ባለፈ በአህጉራዊው መድረክ የመጀመሪያ የጥሎ ማለፍ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት አጫውቷል።

በሩብ ፍጻሜው ኮትዲቭዋር አልጄሪያን ያሸነፈችበትን ጨዋታ በብቃት መምራት ችሏል።

በግማሽ ፍጻሜው ሴኔጋል ቱኒዚያን 1 ለ 0 የረታችበትንም ጨዋታ በዋና ዳኝነት መርቷል።

እ.አ.አ በ2021 በካሜሮን አስተናጋጅነት በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢንተርናሽናል ባምላክ ተሰማ ሶስት ጨዋታዎችን በመሐል ዳኝነት መርቷል።

በምድብ ሁለት ሴኔጋልና ጊኒ ያለ ምንም ግብ አቻ የወጡበትን ግጥሚያ በዋና ዳኝነት መርቷል።

በ16ቱ የጥሎ ማለፍ ዙር ካሜሮን ኮሞሮስን 2 ለ 1 እንዲሁም በግማሽ ፍጻሜው ሴኔጋል ቡርኪናፋሶን 3 ለ 1 ያሸነፈችበትን ጨዋታም መምራት ችሏል።

በተለይም በሴኔጋልና በቡርኪናፋሶ መካከል በተደረገው ጨዋታ ሁለት የጸደቁ ግቦችን በቪዲዮ ቴክኖሎጂ በታገዘ ዳኝነት(ቫር) የሻረባቸው ውሳኔዎችና በአጠቃላይ በጨዋታው ላይ የነበረው ብቃት በወቅቱ አድናቆትን አስችሮታል።

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት ከጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) በአፍሪካ ዋንጫ እንዲያጫውቱ ከመረጣቸው 32 ዋና ዳኞች መካከል ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ይገኝበታል።

ባምላክ ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም በምድብ ስድስት 20 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ላውረን ፖኩ ስታዲየም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ዛምቢያ መካከል አንድ ለአንድ የተጠናቀቀውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መርተዋል።

በጨዋታው ላይ ያሳዩትም ጠንካራ የጨዋታ ብቃት ከስፖርት ቤተሰቡና ተንታኞች አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ዛሬም በምድብ ሶስት ከምሽቱ 2 ሰዓት 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ዴ ላ ፓክስ ስታዲየም ከምድቧ የማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው የአምስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ካሜሮን ከጋምቢያ የምታደርገውን ወሳኝ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራል።

የ43 ዓመቱ ባምላክ በአፍሪካ ዋንጫ በቀጣይ በጥሎ ማለፍ የሚደረጉ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት ይመራል ተብሎ ይጠበቃል። 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫው የተወከለችው በኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ብቻ አይደለም።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ኤሊት ኢንስትራክተር እና የፊፋ ቴክኒካል ኤክስፐርት የሆነው አብርሃም መብራቱ የአፍሪካ ዋንጫው ቴክኒካል ጥናት ቡድን አባል ከሆኑ 19 ግለሰቦች አንዱ ሆኗል።

ኢንስትራክተር አብርሃም ከዚህ ቀደምም በአፍሪካ ዋንጫው በተመሳሳይ ኃላፊነት ላይ ማገልገሉ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮም ከቀድሞ ታላላቅ ተጫዋቾች እና ባለሙያዎች ጋር በቴክኒካል ጥናት ቡድኑ አባልነት እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

ኮሚሽነር ተስፋነሽ ወረታ በካፍ የዳኞች ኮሚቴ አባል በመሆን በውድድሩ ላይ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች። ኮሚሽነር ተስፋነሽ በካፍ ኮሚሽነርነት እየሰሩ ከሚገኙ አራት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አንዷ ናት።

መደምደሚያ 

በጨዋታዎች ላይ በተለይም ጫና ውስጥ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች፣ዘመናዊ እግር ኳስና ዳኝነት የሚፈልገውን ፍጥነት፣የአካል ብቃት፣ቅልጥፍና የስነ ልቦና ዝግጁነት በየጊዜው እያሟላ የሚገኝ ታታሪና ጠንካራ ዳኝ ይሉታል የዳኝነት አመራሮች፣ተንታኞችና የእግር ኳሱ ቤተሰቦች።

ለሙያው ያለው ልዩ ፍቅርና ትጋት አሁን ላለበት ደረጃ አስተዋጽኦ እንዳደረገለት በተደጋጋሚ  ይገልጻል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ በጆሮ ማዳመጫ(ኮምዩኒኬሽን ሲስተም) ዳኞች እንዲግባቡ የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ አድናቆትን አግኝቷል።

እ.አ.አ በ2023 በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አልአህሊ በሜዳው የሞሮኮውን ዋይዳድካዛብላንካን 2 ለ 1 በድምር ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ዋንጫውን ካነሳበት ጨዋታ በኋላ ራሱን ከዳኝነት ማግለሉን ገልጾ ነበር።

ይሁንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ያደረገለትን ጥሪ ተቀብሎ ዳግም ወደ ዳኝነቱ ተመልሷል።

ባምላክ ተሰማ ከእግር ኳስ ዳኝነት በተጨማሪ የነርሲንግ ሙያ ተመራቂ ሲሆኑ በሕክምና ሙያ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የጤና ተቋም ውስጥ በሙያው አገልግሏል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሾሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ባምላክ ተሰማ ገና በልጅነቱ በስነ ፈለክ(አስትሮኖሚ) እውቀቱና ሳይንሳዊ ትንታኔው ብዙዎችን ያስገረመው የሮቤል ባምላክ አባት ነው።

ባምላክ በቀጣይ ዓመታት አሁን ያለውን ብቃት በማሳደግ ፣በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ወዳለው የኢንስትራክተርነት ማማ ከመሸጋገር ባለፈ ሌሎች ስኬቶችና ክብሮችን የሚያገኝበት አጋጣሚ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም