ቀጥታ፡

መንግስት የዜጎቹን ጤና ለመጠበቅ ከሚሰራቸው አበይት ተግባራት መካከል ወቅቱን የጠበቀ የክትባት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ነው - ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት የዜጎቹን ጤና ለመጠበቅ ከሚሰራቸው አበይት ተግባራት መካከል ወቅቱን የጠበቀ የክትባት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ አንዱ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በኮሪያ ሪፐብሊክ ከሚገኘው አለም አቀፍ የክትባት ተቋም ከመጡ ልዑካን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የአለም አቀፍ የክትባት ተቋም የአፍሪካ ቢሮ ለመክፈት ከተመረጡ ሀገራት ኢትዮጵያ እጩ መሆኗ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የልዑክ ቡድኑን አመስግነው የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ጤና ለመጠበቅ ከሚሰራቸው አበይት ተግባራት መካከል ወቅቱን የጠበቀ የክትባት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ለልዑኩ አብራርተዋል።

ይህ ተቋም በአፍሪካ ውስጥ ብሎም በኢትዮጵያ ያለውን ስራ እንዲያጠናክር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚሰራም ዶክተር ሊያ ለልዑኩ አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሰው ክትባት ለማምረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የተቋቋመው የሺልድቫክስ ተቋም ወደ ስራ እንዲገባ የተጀመሩ ስራዎችን እንዲደግፉም ጠይቀዋል።

የአለም አቀፍ ክትባት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጄሮም ኪም በበኩላቸው ቢሮውን በአፍሪካ ከመክፈት ባለፈ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት የክትባት ምርት እንዲሰፋ የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ብለዋል።

ድጋፉንም በስልጠና፣ በምርምርና በሌሎች ጉዳዮች በማቀናጀት ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር የተጀመረውን አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱም የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት መካፈላቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም