ግንባታቸው ለተጓተቱና ለተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ግንባታቸው ለተጓተቱና ለተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ
አዲስ አበባ ፤ ጥር 13/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ግንባታቸው ለተጓተቱና ለተቋረጡ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙን የ2016 በጀት አመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳሬክተር ኢንጅነር መሃመድ አብዱራህማን በግማሽ ዓመቱ በመንገድ ጥገና፣ በአዳዲስ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የተከናወኑ ዋና ዋና የእቅድ አፈጻጸምን ሪፖርት አቅርበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች መዘግየት፣ የካሳ ክፍያ፣ የስራ ተቋራጮች አቅምና ሌሎች ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ጥያቄ አንስተዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር፣ በተጋነነ የካሳ ግምት፣ በተቋራጮች አቅም ማነስና በተለያዩ ምክንያቶች ፕሮጀክቶች በጊዜያዊነት መቆማቸውን በሪፖርት መቅረቡንም ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም እነዚህና ሌሎች በጀት ተይዞላቸው ግንባታቸው ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን መፍትሄ ለመስጠት የተያዘውን አቅጣጫምን እንደሆነ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
እንዲሁም ለረዥም ጊዜ የተጓተቱ እና ግንባታቸው ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ምን አይነት እርምጃ እየተወሰደ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የስራ ተቋራጮች አቅም ማነስ በመሆኑ ይህን ለማስተካከል ምን አይነት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ተነስቷል፡፡
የተቋሙ ሃላፊዎች በተለያዩ ምክንያት የተቋረጡ፣ የተጓተቱና ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ችግር ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።
ምክትል ዋና ዳሬክተሩ ኢንጅነር ደጀኔ ፍቃዱ ፕሮጀክቶችን ስራ ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅድ በማውጣት እየተሰራ መሆኑን በምላሻቸው አብራርተዋል።
ከካሳ ክፍያ፣ ከስራ ተቋራጮች አቅም ማነስ፣ ከግብአት አቅርቦት፣ ወሰን ማስከበርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ሃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ ተቋሙ የሰራተኞችን አቅም ለማጎልበትና ዘመናዊ አሰራርን ለመዘርጋት እያከናወነ ያለውን ተግባር በጥንካሬ በማንሳት በትኩረት መሰራት ያለባቸው ጉዳዮችን ዘርዝረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ለተጓተተ፣ ተጀምረው ለተቋረጠና ለቆሙ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደ ስራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ለመንገድ ግንባታ መዘግየት ከፍተኛ ችግር በመሆን በተለያየ ጊዜ እልባት እንዲሰጠውና እስካሁን መፍትሄ ያላገኘው የካሳ ክፍያ በቀጣይ 6 ወራት እልባት እንዲያገኙም አስገንዝበዋል፡፡