የባህር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ምሁራን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ምሁራን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተመለከተ
ድሬዳዋ፤ ጥር13/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያውያን የባህር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ምሁራን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተመለከተ።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ "የባህር በርና ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች" በሚል መሪ ሃሳብ ከባለድርሻ አካላትና ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጋር በባህር በር አስፈላጊነት ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
ዛሬ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁራን፣ የፖለቲካ ሣይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች "የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ፣ የባህር በር ጥያቄው ከዓለም አቀፍ ህግ አኳያ" በሚሉ ርዕሶች ጥናታዊ ፅሁፎች አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም እንደተናገሩት፤ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህግም ተቀባይነት ያለው ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት በመሆኗ ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብት ችግሮች እንድትጋለጥ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ይህን ችግር ለመፍታትና የአገራችንን የህልውና ዋስትና የሆነው የባህር በር ጥያቄ ተገቢው ምላሽ እንዲያገኝ ምሁራን በዕውቀት ላይ ተመስርተው "ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የጀመሩትን የማሳወቅ ተግባራት አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል" ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተማም አወል ኢትዮጵያ በየዓመቱ ብዙ ቢሊዬን ብር ለወደብ ኪራይ እንደምታወጣ ገልጸው፤ ይህን ችግር በመፍታትና ሁለንተናዊ ዕድገቷን ለማስቀጠል ብሎም የዜጎቿን ህይወት ለመለወጥ የባህር በር ጥያቄዋ እንዲመለስ መስራት የዚህ ትውልድ ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት መሆኑንም አብራርተዋል።
በተለይም እየተመዘገበ ያለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ቀጣይነት የሚረጋገጠው የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል ዲን ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ህዝብ፣ ሰፊ መልክዓ ምድርና ኢኮኖሚ ያላት ብትሆንም የባህር በር የሌላት ብቸኛ ታላቅ አገር መሆኗን አስታውሰዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ አገራችን ያነሳቸው የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ የባህር በር ህግ መሠረት ምላሽ ማግኘት የሚያስችላት በመሆኑ ተቀናጀቶ መረባረብ ይገባል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከሶማሊ ክልል የአገር ሽማግሌ አቶ መሐመድ ሙሴ በበኩላቸው፤ አገራችን የጀመረችው የባህር በር ጥያቄ የዜጎች ሁሉ መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህን ዕውን ማድረጊያው አንዱ መንገድም የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ያላቸውን "የህዝብ ለህዝብ ትስስር በመጠቀም የጋራ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራ መሰራት አለበት" ብለዋል።
መንግስትም ከተጎራባች አገሮች ጋር በተለይም ከሶማሊያ አገርና ከማህበረሰብ መሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትና የጋራ ዕድገትን አንግቦ በመስራት ጥያቄው እንዲሳካ ማድረግ እንደሚገባ አክለዋል።