በአማራ ክልል ከ276 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወሰዱ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ276 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወሰዱ
ጎንደር ፤ ጥር 13 / 2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ከ276 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
''ጎንደር ታምርት፤ አምርታም ትጠቀም'' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ ተካሂዷል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዮሃንስ አማረ እንደተናገሩት፤ ክልሉ የፀጥታ ችግር ቢያጋጥመውም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ አልተቋረጠም፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት 1 ሺህ 282 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ ወደ ግንባታ ሲገቡም ለ226 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድሎች እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል፡፡
ባለሃብቶቹ ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ቀደም ሲል ፈቃድ የተሰጣቸው 417 ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በመሰማራት በተለያዩ የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም አውስተዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመፍታት በተደረገ ጥረትም 300 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት በመመደብ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት የማሟላት ስራዎች መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም 25 የሚሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችና የ"ሆሊቲካልቸር" ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት እንደቻሉም አስረድተዋል፡፡
''ፎረሙ የጎንደር ከተማን የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ተወያይቶ በመፍታት የከተማውን ኢንቨስትመንት ለማሳለጥ ያለመ ነው'' ያሉት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው፡፡
ጎንደር ከተማ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተመራጭ መሆንዋን ጠቅሰው፤ በአካባቢው በስፋት የሚመረቱ የቅባት እህል፣ ጥጥና የቅመማ ቅመም ሰብሎችን ለሚያቀናብሩ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም በበኩላቸው፤ በከተማው በሚገኙ አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች ከ200 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች በተለያዩ የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ከመካከላቸውም 58 ያህሉ ወደ ምርት ስራ በመግባት ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመው፤ 31 ፕሮጀክቶች ደግሞ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በከተማው በማኑፋክቸሪንግ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርና፣ በእንስሳት ሀብት ልማትና በግብርና መሳሪያዎች አቅርቦት ለመሰማራት የሚያስችሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ተመስገን መኮንን በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ የከተማ አስተዳደሩ የባለሀብቶችን ችግር በቅርበት ተረድቶ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በኩል አበረታች ተግባር እያከናወነ ነው።
በተለይም ከተማ አስተዳደሩ የመሬት አቅርቦትና ከቀረጥ ነፃ እቃዎችን ከውጭ እንዲያስገቡ ተገቢውን እገዛ በማድረግ ለዘርፉ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ አቅርበዋል፡፡
በፎረሙ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት እንዲሁም በከተማው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡