ኢትዮጵያ በቀጣናው የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መርህ አድርጋ እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቀጣናው የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መርህ አድርጋ እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናው የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መርህ አድርጋ እየሰራች መሆኑን በኬንያ፣ በሶማሊያ እና በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።
ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የባህር በር ስምምነትም የሰጥቶ መቀበልና በጋራ የመልማት ዕቅድ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲና በጋራ ልማት ዙሪያ ቀጣናዊ ብሎም አህጉራዊ ትስስር ለመፍጠር እያከናወነች ያለውን ሥራ በተመለከተ ኢዜአ በኬንያ፣ በሶማሊያ እና በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችን አነጋግሯል።
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናውም ይሁን አጠቃላይ በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ልማት እንዲረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የመሠረተ-ልማትና የንግድ ትስስር በመፍጠር ረገድ እያከናወነቻቸው ያሉ ተጨባጭ ሥራዎችን ዘርዝረዋል።
የትኛውንም መሠረተ-ልማቶችም ሆነ በጋራ የመልማት እሳቤዋን ተግባራዊ የምታደርገው ባስቀመጠችው ግልጽ ፖሊሲ ላይ መሠረት በማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት የሚል መርህ የሚከተል መሆኑን አንስተው፤ በዚሁ መንገድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገና የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ ነው ብለዋል።
በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ሙክታር መሃመድ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፍላጎቷን በተግባር በማስደገፍ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም የጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደረጉ የልማት ሥራዎችን በልዩ ትኩረት እያከናወነች መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ሶማሊያን ጨምሮ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ቁርጠኛ አቋም ይዛ እየሰራች ነው ብለዋል አምባሳደሩ።
ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የባህር በር ስምምነትም የሰጥቶ መቀበልና በጋራ የመልማት ዕቅድ መሆኑን አስረድተዋል።
ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮ-ጂቡቲ ወዳጅነት በጋራ ልማትና ተጠቃሚነት በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ገልፀዋል።
ሁለቱ ሀገሮች በመንገድ፣ በባቡር፣ በወደብ፣ በውሃ፣ በኤሌክትሪክና ሌሎች ዘርፎች በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ይበልጥ ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ መካከል የተደረገው የባህር በር ስምምነት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወቃል፡፡