የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ መሬትን በአግባቡ መጠቀም እንድንችል ያግዘናል -- በድሬዳዋ የገጠር ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ መሬትን በአግባቡ መጠቀም እንድንችል ያግዘናል -- በድሬዳዋ የገጠር ነዋሪዎች
ድሬደዋ ፤ጥር 13/2016(ኢዜአ)፦በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዘጋጀው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ መሬትን በአግባቡ መጠቀም እንድንችል ዕድል ይፈጥርናል ሲሉ በውይይቱ የተሳተፉ የድሬዳዋ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከገጠር ህብረተሰብና ከባለድርሻ አካላት ጋር ግብአት ያሰባሰበበት ውይይት መድረክ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እያካሄደ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁ የመሬት ሃብትን በአግባቡ በመመዝገብ፣ በማስተዳደር እንዲሁም መሬት ላይ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ህጋዊነት ተላብሰው ተግባር ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
ይህም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ይዞታውን በሚገባ በማልማት ተጠቃሚ የሚሆንበት መሆኑም እንዲሁ።
በድሬደዋ በተካሄደው ውይይት ላይ ከተሳተፉት አርብቶ አደሮች መካከል አቶ አብዱረህማን ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ረቂቅ አዋጁ “አርብቶ አደሮች ከከብት እርባታ ጎን ለጎን ወደ ማምረት እንዲሸጋግሩ ያግዛል” ።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አርሶ አደር አብደላ ኢብራሂም በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ቀደም ሲል አርሶ አደሮች በልማትና በኢንቨስትመንት ስም በትንሽ ገንዘብ ከመሬታቸው ተፈናቅለው ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ የነበረውን አካሄድ ይለውጣል ሲሉ ገልጸዋል።
''በይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ተበድረንና ግብአት በማሟላት ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችለናል'' ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ''ከድህነት ለመውጣት በምናከናውነው ተግባራት ውጤታማ ያደርገናል” ሲሉም አክለዋል።
ረቂቅ አዋጁ የሴቶችና የወጣቶችን የመሬት ተጠቃሚነት በአግባቡ የሚያረጋግጥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሃርላ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሳፊያ ሀሰን ናቸው።
በመሆኑም የረቂቅ አዋጁን ጥቅሞች ለተቀረው የገጠር ነዋሪዎች ማስተማርና ማሳወቅ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ያስችላል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ ረቂቅ አዋጁ የመሬት አጠቃቀምን በማዘመን የገጠሩን ማህብረሰብ ህይወት ለመለወጥ መሠረታዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ለጢፋ አባተማም በበኩላቸው ውይይቱ ለረቂቅ አዋጁ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ግብኣቶች እየተሰበሰበበት መሆኑን ተናግረዋል።