ቀጥታ፡

የደም ልገሳ ባህልን ለማሳደግ ለኮሙኒኬሽንና ለህዝብ ግንኙነት ስራ ትኩረት ተሰጥቷል-- የደምና ህበረሕዋስ አገልግሎት

አዳማ ፤ ጥር 13/2016(ኢዜአ)፦ የደም ልገሳ ባህልን ለማሳደግ ለኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ስራ ትኩረት መስጠቱን የደምና ህበረሕዋስ አገልግሎት አስታወቀ።

የኮሙዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነትባለሙያዎች በደምና ህበረሕዋስ አገልግሎት ላይ ተገቢውን ግንዛቤ አግኝተው በሙያቸው እንዲያግዙ ለማስቻል ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ የደምና ህብረሕዋስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት ህበረተሰቡ ደም በመለገስ የተጎዱ ዜጎችን ህይወት መታደግ እንዲችል የኮሙዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ስራ ወሳኝ ነው።

በተለይ ከበጎ ፍቃድ ደም ለጋሾች ባለፈ የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ ኮሙዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ስራ ይጠናከራል ብለዋል።

አገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽና ህዝብ ግንኙነትአደረጃጀትና መዋቅር እስከ ደም ባንክ ቅርንጫፎች ለመዘርጋት የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርጾ እየተገበረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም በደምና የአይን ብሌን አሰባሰብ ላይ ከግንዛቤ ክፍተት ጀምሮ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የየአካባቢ ባህልና ቋንቋ መሰረት ያደረገ የኮሚዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ስራ ይከናወናል ነው ያሉት።

የዛሬው የውይይት መድረክም በመልዕክት ቀረፃና የተግባቦት ሂደት ላይ የተሻለ አሰራር ለመከተል የሚያስችል ግብዓት የሚሰበሰብበት ነው ብለዋል።

ደም መለገስ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ  አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች፣ ህፃናትና የእናቶችን ህይወት በመታደግ ረገድ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍል ደም የመለገስ ልምዱን እንዲያሳድግም ጠይቀዋል።

አገልግሎቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ169 ሺህ ዩኒት በላይ ደም በመሰብሰብ የዕቅዱን 84 በመቶ ማሳካቱን የገለፁት ደግሞ የአገልግሎቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ታዬ ናቸው።

በዚህ ረገድ ኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም ድሬ ደዋ፣ አዲስ አበባና አሶሳ ከተሞች የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው ተናግረዋል።

ነገር ግን በጤና ተቋማት ከሚታየው የደም ፍላጎት አንፃር አሁንም ደም አሰባሰብ ላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ በስፋት መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በዚህም የኮሙዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ የደም አሰባሰብ ሂደቱን በሙያቸው እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

''በአይን ብሌን ላይ የሚሰሩ ስራዎችንም እንዲያግዙ ጭምር እየሰራን ነው'' ያሉት አቶ ሀብታሙ አገልግሎቱ ህዝቡ ዘንድ ተደራሽ ለመሆን የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግኑኝነት ስራ በሙሉ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በዚህም በቀጣይ ስድስት ወራት ዕቅዱን ለማሳካት የሚያግዙ የኮሙዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ስራ በስፋት ለማከናወን መታቀዱንም አስረድተዋል።

በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከፌዴራልና ክልሎች የተወጣጡ ኮሙዩኒኬሽናነ የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሙያተኞች ተሳታፊ ሆኖዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም