ቀጥታ፡

ረቂቅ ዓዋጁ አርሶና አርብቶ አደሮችን  ተጠቃሚ በማድረግ በአገር ደረጃ  የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት  ያግዛል

ሰመራ፤ ጥር 13/2016(ኢዜአ)፡- የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ ዓዋጅ አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ በአገር ደረጃ  የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተገለጸ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በአፋር ክልል ምክር ቤት አስተባባሪነት  በረቂቅ ዓዋጁ ላይ በሠመራ ከተማ  ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት ማካሄድ ተጀምሯል።

የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የውይይቱ አስተባባሪ አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ በዚህ ወቅት እንዳስረዱት፤ ረቂቅ ዓዋጁ አርሶና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላቸዋል።


 

የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ አገሪቱ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር በማጣጣም በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስችልና በአገር ደረጃ  የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው ዓዋጅ ከአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ያልተጣጣመና በየጊዜው ከነበሩት ለውጦች ጋር ሊጓዝ ያልቻለ እንደነበርም አቶ ዘካሪያስ አስታውሰዋል።

ረቂቅ ዓዋጁ የመሬት ሃብትን በአግባቡ በመመዝገብና በማስተዳደር እንዲሁም መሬት ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ህጋዊነት ተላብሰው እንዲከናወኑ ለማድረግ ታልሞ መረቀቁንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮችን በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ዕውቅና ስለሚሰጥ በዝርዝር ህጎች ተደግፎ  ሥራ ላይ ሊውል ይገባዋል ብለዋል።

አርብቶ አደሩ መሬቱን ሥራ ላይ ለማዋል ሲፈልግ ህጋዊነትን ይዞ በአግባቡ ለማስተዳደር እንደሚያስችለው አስተባባሪው ተናግረዋል።

''የተፈጥሮ ሐብታችንን በአግባቡ በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ሥርዓት መኖሩ አስፈላጊ ነው፤ ይህም የአገራችንን ሥነ ምህዳር ያገናዘበ ዘላቂ የገጠር ልማት ዕቅድ ለማውጣት የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

የአፋር ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ መይረም መሐመድ በበኩላቸው፤ የውይይቱ ተሳታፊዎች ረቂቅ ዓዋጁ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ዳብሮ እንዲወጣ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በውይይቱ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ ባለድርሻ አካላትና የኅብረተሰቡ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ውይይቱ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም