ቀጥታ፡

አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በመስኖ ልማት ላይ በመሰማራቱ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው

ጂንካ ፤ ጥር 13/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ አርብቶ አደሮች ከእንስሳት እርባታው ጎን ለጎን በመስኖ ልማት በመሰማራት በኑሮአቸው ላይ ያመጡትን ተጨባጭ ለውጥ ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

 የፌዴራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ደሌኙመር ቀበሌ በአርብቶ አደሮች እየለሙ ያሉ የመስኖ ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የውሃና ማዕድን ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በክልሉ ዝናብ አጠር በሆኑ አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚተገበሩ የግብርና ስራዎች ለውጦች ማሳየታቸውን ገልፀዋል።


 

አርብቶ አደሩ የኑሮው መሰረት ከሆነው የእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን የሚያከናውናቸው የመስኖና የእርሻ ልማት ስራዎች በኑሮአቸው ላይ ተጨባጭና አስደሳች ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል ።

ይህን በማጠናከር አርብቶ አደሩ በሰፊው እንዲሳተፍና ዘላቂ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ክልሉ አበክሮ እንደሚሰራ ኢንጂነር አክሊሉ ተናግረዋል ።

አርብቶ አደሩ በግብርና ልማቱ ላይ ለመሳተፍ እያሳየ ያለው ተነሳሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀው በአገልግሎት ላይ ያሉ አነስተኛ የመስኖ ልማት መሳሪያዎች በነዳጅ የሚሰሩ በመሆናቸው ፍላጎቱን ማሟላት እንዳልተቻለ አንስተዋል ።

በክልሉ በአርብቶ አደር አካባቢ ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል ለም መሬትና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንዳሉ አውስተው በቀጣይ እነዚህን ሀብቶች አቀናጅቶ በማልማት በአርብቶ አደሩ ኑሮ ላይ የታዩ ለውጦችን በዘላቂነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለአብነት በነዳጅ ሀይል የሚሰሩትን የመስኖ መሳሪያዎች በሶላር ኢነርጂ ለመቀየር ትኩረት የተሰጠበት መሆኑን አንስተው ለዚህም የክልሉ መንግስት የአዋጭነት ጥናት እያካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም አርሶ አደሩ ለነዳጅ የሚያወጣውን ወጪ በመቀነስ በሌሎች የግብርና ልማቶች ላይ በማዋል የተጀመረውን የግብርና ስራ በስፋት እንዲያከናውን ይረዳል ብለዋል ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ በበኩላቸው በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚተገበሩ የግብርና ልማት ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን አስገኝተዋል።


 

ቀደም ሲል አርብቶ አደሩ በእንስሳት እርባታው ላይ ብቻ ኑሮው በመመስረቱ ድርቅ በተከሰተ ወቅት ለቀውስ እንደሚጋለጥ አስረድተዋል።

አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታው ጎን ለጎን በሰብል፣ በፍራፍሬና በመኖ ልማት ላይ በመሰማራት በድርቅ ወቅት የሚከሰቱ ቀውሶችን መቋቋም የሚያስችል አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

በወረዳው በዴለኙመር ቀበሌ በመስኖ ልማት ከተሰማሩ አርብቶ አደሮች መካከል ጉዶ ሎቸርዮ አንዱ ሲሆኑ 82 አባላት ያለው ማህበር በመመስረት በ270 ሄክታር ማሳ ላይ ላይ መኖ በኩታ ገጠም እያለሙ እንደሆነ ገልፀዋል።

መኖን ማልማት በመጀመራቸው በድርቅ ወቅት የሚከሰተውን የእንስሳት ሞት ለመከላከል እንደቻሉም ተናግረዋል።

''የመኖ ልማቱ ከብቶቻችንን ከመመገብ ባለፈ ምርቱን በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ እያገኘንበት ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አርብቶ አደር ኛሌ ኞክቻ ናቸው።

አቶ ኞሌ እንደሚሉት በቀጣይ የበጋ ወራት ምናልባት ድርቅ ቢከሰት በመኖ ማቀነባበሪያ አማካኝነት በመጋዝን ውስጥ መኖ እያከማቸን ነው ብለዋል።

በመኖ ልማቱ ጥሩ ውጤት እንዳገኙበት ገልፀው በክልሉ መንግስት ድጋፍ ከሰብልና፣ ከፍራፍሬ ልማቱ ጎን ለጎን መኖ በስፋት እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታውም የፌዴራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የአካባቢው አርብቶ አደሮች ተሳትፈዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም