ኢትዮጵያ የ28ኛውን የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ውሳኔዎችን ለመተግበር ከአጋር አካላት በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት- የፕላንና ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የ28ኛውን የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ውሳኔዎችን ለመተግበር ከአጋር አካላት በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት- የፕላንና ልማት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2016(ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን ለመተግበርና በትግበራ ሂደት ከሁሉም አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ እአአ ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2023 ዓ.ም በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አዘጋጅነት በዱባይ ከተማ ሲካሄድ የቆየውን 28ኛውን የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በጉባኤው ኢትዮጵያ ከመሪዎች እስከ በዝርዝር በተካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች፤ በጎንዮሽ በተካሄዱ የሁለትዮሽና የባለብዙ ውይይቶች እንዲሁም እየተከናወኑ ባሉ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ኤግዝቢሽን እና ተያያዥ ጉዳዮች ስኬታማ ተሳትፎ አድርጋ መመለሷን ገልጿል።
ጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ ድርድር በርካታ ውጤቶች የተገኙበት እንደነበርና ኢትዮጵያ በመሪነት መሳተፏን በመግለጫው አስገንዝቧል።
እንደ ሀገር ከምታደርገው ተሳትፎ ባለፈ አባል በሆነችባቸው የአፍሪካ ቡድን እና በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ቡድኖችን በመምራት መሳተፏን ገልጾ አፍሪካውያን በአንድ ድምጽ እንዲደራደሩና ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁ አስተባብራለች ብሏል።
የጉባኤው ፕሬዝዳንት በሆነችው የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አስተባባሪነት የተዘጋጁ ለጉባኤው ውሳኔዎች አጋዥ የሆኑ በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በጤና፣ ግጭት ማስወገድና ሠላም፣ ሁሉን አቀፍ የባለድርሻዎች የትብብር ማዕቀፍ የተመለከቱ ስምምነቶችን ፈርማ መቀላቀሏንም አስገንዝቧል።
ከዋና ጉባኤ ጎን ለጎን በአጠቃላይ 15 ከሚሆኑ አጋር ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ የሁለትዮሽ ትብብሮችን አጠናክሮ ለመቀጠልና አዳዲስ ተነሳሽነቶችን በመቅረጽ በጋራ ለመስራት ከስምምነት መደረሱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው አመላክቷል።