ቀጥታ፡

ምሁራን የባህር በር ጥያቄን ተገቢነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል- ዶክተር ተማም አወል

ድሬዳዋ፤ ጥር 13/2016 ( ኢዜአ) ምሁራን ያላቸውን ዕውቀት በመጠቀም የባህር በር ጥያቄን ተገቢነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ተገቢ መሆኑን የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተማም አወል ተናገሩ።

በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት "የባህር በር ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር በር አስፈላጊነት ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የድሬዳዋ ዩኒቪርስቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተማም አወል እንደተናገሩት የኢትዮጵያውያን የባህር በር ጥያቄ በአለም አቀፍ ህጎች ጭምር ተቀባይነት ያለው የዜጎች የህልውና ጥያቄ ነው።

በተለይ የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን የመኖርና እንደ አገር የመዝለቅ መሠረታዊ አጀንዳ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የምታደርገው ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የባህር በር ጥያቄ በአለም አቀፍ ህጎችም ሆነ በሰጥቶ መቀበል መርህ እውን እንዲሆን መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ምሁራን ያላቸውን ዕውቀት በመጠቀም የባህር በር ጥያቄን ተገቢነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ያዘጋጀው መድረክም አገራችን ያላት ታሪካዊ የባህር በር ባለቤትነት ብቻ ሳይሆን የባህር በር ጥያቄያችን በአለም አቀፍ ህጎች ጭምር ተቀባይነት ያለው መሆኑን ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን አውስተዋል።

የባህር በር ጥያቄው በዘመናት ቅብብሎሽ በህዝብ ውስጥ የሚመላለስ መሠረታዊና ወቅታዊ ጥያቄ መሆኑን ለማሳወቅም ጭምር ነው ብለዋል።

"የባህር በር ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች" በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የሲቪክ ማህበራት፣ የህብረተሰብ ተወካዮችና የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በመድረኩ ላይም ''የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከአለም አቀፍ ህግ አንፃር''፣ ''የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ" በሚሉ ርዕሶች የውይይት መነሻ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግበትም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም