ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የመሰረተ ልማት አማራጮችን ለማቅረብ የምትተጋው የጋራ ተጠቃሚነትን ስለምታስቀድም ነው - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ውሃና ታዳሽ ኅይልን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አማራጮችን ለማቅረብ የምትተጋው የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ስለምታስቀድም መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደምትጥረው ሁሉ ፍላጎቶቿን ለማሟላት በምታደርገው እንቅስቃሴ መታገዝ እንዳለባትም ገልጸዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እና በድሬዳዋ የጅቡቲ ቆንስላ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሙሳ ሃጂ ጀማል የተመሩ የሁለቱ ሀገራት ልዑካን በሶማሌ ክልል አዲጋላ እና አካባቢው ተዘዋውረው የኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር ዘለል የንጹህ ውሃ ፕሮጀክት እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ያላት ዋነኛ ፍላጎት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ነው።

በዚህም ምክንያት ከጎዶሎዋ በመቀነስ ጭምር የጋራ ማንነት የሚጋሩ ህዝቦች ያሏቸው አገራት በትብብር እንዲለሙ የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

ለአብነትም የቀጣናው የመጠጥ ውሃ እና የታዳሽ ሃይል ፍላጎት እንዲሟላ ያላትን ጸጋዎች እያለማች ለጎረቤቶቿ እያጋራች መሆኑን አንስተዋል።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ለባህር ቅርብ የሆነች ትልቅ ሀገር ብትሆንም የባህር በር አለመኖሩ የልማት ፍላጎቷ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደምትጥረው ሁሉ ፍላጎቶቿን ለማሟላት በምታደርገው እንቅስቃሴም መታገዝ አለባት ነው ያሉት።

የባህር በር ለማግኘት በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በቅጡ ያልተረዱ አካላትም የኢትዮጵያ ፍላጎት የጋራ ልማት መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የታዳሽ ኅይል አማራጮችን ለጎረቤቶቿ በማቅርብ አጠቃላይ ልማታቸው እንዲያፋጥኑ ያላትን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ገልጸው፣ ጎረቤት ሀገራትም የየባህር በር ጥያቄና የወደብ ክፍያ ጉዳይ  ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ውሃ ለቀጣናው ትስስር መሰረታዊ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወንዞች ወደጎረቤት ሀገራት እየፈሰሱ ሀገራቱን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትፈልገው በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ መልማት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ችግሮችን እና ጸጋዎችን ተጋርቶ መበልጸግ ይገባል ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም